በጋሞ ዞን በበልግ አዝመራ ከ125 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጋሞ ዞን በበልግ አዝመራ ከ125 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው
አርባ ምንጭ፤ የካቲት 19/2018 (ኢዜአ)፡- በጋሞ ዞን በበልግ አዝመራ ከ125 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች በማልማት ምርታማነትን ለማሳደግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
የዞኑ አርሶ አደሮች በበኩላቸው በበልግ አዝመራ የግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸውን በማሳደግና አስፈላጊውን ግብዓት በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በጉራጌ ዞን በበጋ መስኖ ወደ 27 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለምቷል
የጋሞ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ሃላፊ አቶ ወርቅነህ ካልሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በበልግ አዝመራ ምርታማነትን ለማሳደግ ከማሳ ልየታ ጀምሮ በግብአት አቅርቦት በቂ ዝግጅት ተደርጓል።
በበልግ አዝመራ ከ125 ሺህ 897 ሄክታር በላይ መሬት በአዝርዕት፣ በሆርቲካልቸርና በዓመታዊ ሰብሎች እንደሚሸፈን ገልጸው፣ በዚህም ከ17 ሚሊዮን 843 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዷል ብለዋል።
በልማቱም ምርታማነትን ለማሳደግ በተለይ በሞዴል አርሶ አደሮችና በግብርና ሠርቶ ማሳያዎች የክህሎት ማሳደጊያ ስልጠና ለአርሶ አደሩ መሰጠቱን ጠቁመዋል።
በበልግ ከሚለማው መሬት ከ75ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው መሬት በኩታ ገጠም እንደሚለማ ጠቁመው፣ ለልማቱም ከ156ሺህ ሄክታር በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ቀርቧል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ወርቅነህ ገለጻ፤ በአርሶ አደሮችና በባለሀብቶች እጅ ያሉ ከ84 በላይ ማረሻ ትራክተሮችን በማቀናጀት ከ52 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በሜካናይዜሽን ይለማል።
በዞኑ በምዕራብ አባያ ወረዳ ፉራ ቀበሌ ሞዴል አርሶ አደር ሮባ ሎላሶ በበኩላቸው፤ በበልግ አዝመራ ምርታማነታቸውን ለማሳደግ የሚያስችሉ የክህሎት ስልጠና እንዳገኙ ገልጸዋል።
አስር ሄክታር መሬታቸውን በትራክተር ታግዘው ደጋግመው በማረስ ማለስለሳቸውን ገልጸው በአሁኑ ወቅትም ማሾ፣ በቆሎ፣ ሱፍና ጤፍ ለመዝራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ለልማቱ በግብርና ባለሙያዎች ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸው፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግም አስፈላጊ ግብአቶችን በመጠቀም ልማቱን እንደሚያከናውኑ አስታውቀዋል።
በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የጫኖ ጫልባ ቀበሌ አርሶ አደር አለሙ ማሜጫ ፣ የግብርና ልማት ሥራቸው በምግብ እህል የቤተሰባቸውን ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ ከምርት ሽያጩ ሀብት ለማፍራት መቻላቸውን ተናግረዋል።
በበልግ አዝመራ አስፈላጊውን ግብአትና የግብርና ቴክኖሎጂ በመጠቀም የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ ጠንክረው እየሠሩ መሆኑንም ገልጸዋል።