ቀጥታ፡

በጉራጌ ዞን በበጋ መስኖ ወደ 27 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለምቷል

ወልቂጤ፤ የካቲት 18/2018(ኢዜአ)፡- በጉራጌ ዞን በበጋ መስኖ ወደ 27 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መልማቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት ከፍተኛ ለውጥ እየተመዘገበ ነው-ግብርና ሚኒስቴር

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ እና ግብርና መምሪያ ኃላፊ አበራ ወንድሙ እንዳሉት፣ በተያዘው በጋ ወቅት 26ሺህ 781 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በመስኖ መልማቱንና ከ6 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

በእስካሁኑ ሂደትም 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን አስረድተዋል።


 

በዞኑ የተለያዩ የሰብል እና የአትክልት ዓይነቶች በጥራትና በብዛት እየተመረቱ መሆኑን ገልፀው በአካባቢው ከዚህ ቀደም ተመርተው የማያውቁ እንደ ጥቁር አዝሙድ እና ኮረሪማ ያሉ የቅመማቅመም ዓይነቶች እየተመረቱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዞኑ አበሽጌ ወረዳ የፈንጣ ቀበሌ አርሶ አደር ሙሃጅር በድሩ ከአራት ዓመታት ወዲህ እየተሳተፉባሉበት ያለው የበጋ መስኖ ልማት ኑሯቸውን በመለወጥ ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ማሳደጉን ገልፀዋል።


 

ዘንድሮም የተመቻቸላቸውን እድል በመጠቀም በሁለት ሄክታር መሬት ላይ የዘር ሽንኩርት በመስኖ እያለሙ መሆናቸውንና የተሻለ ምርት ለማግኘት እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ከዝናብ ጥገኝነት ወጥተው በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ በመስኖ በማልማት ተጠቃሚ በመሆናቸው ወደ ዘርፉ መግባታቸውን የተናገሩት ደግሞ በቸሃ ወረዳ የአዘርናሲሰ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ዘመቻ አሰና ናቸው።


 

መንግስት ባመቻቸላቸው የእርሻ መሬት፣ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ እና የሙያ ድጋፍ በመታገዝ ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን የተሻለ ደረጃ ላይ ማድረስ መቻላቸውን ገልጸዋል።

መስኖ በስፋት እና በውጤታማነት ማምረት እንደሚቻል ለአካባቢው ህብረተሰብ ግንዛቤን በመፍጠር ረገድ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸው በአካባቢው ታርሶ የማያውቅ መሬትን ወደ ምርታማነት ቀይረናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም