ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ግብ እንዲሳካ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች ትገኛለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ግብ እንዲሳካ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች ትገኛለች
ድሬዳዋ፤ የካቲት 19/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ግብ እንዲሳካ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት መምህርና ተመራማሪ ዘሪሁን ተምሳስ(ዶ/ር) ገለፁ።
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት መምህርና የዘርፉ ተመራማሪ ዘሪሁን ተምሳስ(ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ ከወዲሁ እያከናወነች የምትገኘው ዘርፈ ብዙ የልማት እንቅስቃሴዎች ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ ነው ብለዋል።
ለአብነትም ባለፉት ዓመታት በማምረቻው ዘርፍ እየተመዘገቡ የሚገኙ ውጤታማ ስራዎች የህብረቱን የኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ሽግግር ማሳካት የሚያስቻሉ መሆናቸውን አንስተዋል።
ግዙፍ የውጭ ሀገራት ኢንቨስተሮች በተለያዩ ከተሞች በተገነቡ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና የኢንዱስትሪ ፓርኮች እያከናወኑ የሚገኙትን ልማቶችን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ሌላው ለህብረቱ አጀንዳዎች መሳካት አስተማማኝ መሠረትና መደላደል እየጣለች መሆኗን ከሚያረጋግጡ ተግባራት መካከል በግብርናው በተለይም በስንዴ ልማት ላይ የተገኘውን ውጤት አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በዲጂታል ትስስርና በመሠረተ ልማት አስደናቂ ሥራ እያከናወነች ነው
ይህም የአፍሪካ ህብረት ሀገራት ያላቸውን ፀጋና ዕውቀት ተጠቅመው የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ጉዞ ማሳካት እንደሚችሉ ትልቅ ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከእነዚህ ሁሉ ባሻገር በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በመሠረተ ልማት ዘርፎች እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶች የአፍሪካ ሀገራትን ያስተሳሰሩና ኢኮኖሚያዊ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋገጡ ናቸው ብለዋል።
በተለይም ግዙፉ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ ዘመናዊ የባቡርና የመንገድ መሠረተ ልማቶች በቀጣናው ሀገራት እየፈጠሩ የሚገኙትን ውህደትና የጋራ ተጠቃሚነትን አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ ለህብረቱ አጀንዳዎች መሳካት በምሳሌነት እያከናወነቻቸው ያለችው ተግባራትን ይበልጥ ለማሳደግ እየተተገበሩ የሚገኙ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ምቹ መደላድል የሚፈጥሩ መሆናቸውን አመላክተዋል።