ኢትዮጵያ በዲጂታል ትስስርና በመሠረተ ልማት አስደናቂ ሥራ እያከናወነች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዲጂታል ትስስርና በመሠረተ ልማት አስደናቂ ሥራ እያከናወነች ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 17/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በዲጂታል ትስስርና በመሠረተ ልማት አስደናቂ ሥራዎችን እያከናወነች መሆኑን በኢትዮጵያ የፊንላንድ አምባሳደር ሲኒካ አንቲላ ገለጹ።
አምባሳደር ሲኒካ አንቲላ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያና ፊንላንድ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ዲጂታል ሉዓላዊነቷን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነች ነው
ፊንላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የትምህርት ዘርፉን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ጠንካራ የልማት ትብብር እንዳላት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በአካባቢ ጥበቃ እና በዲጂታል ትስስር ረገድ ስኬታማ ሥራዎች እየሠራች መሆኑንም አንስተዋል።
እንዲሁም በመሠረተ ልማት ግንባታ እያከናወነቻቸው ያሉ ስራዎች የሚደነቁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ፊንላንድ በአካታች ትምህርት እና በማህበረሰብ አቀፍ የገጠር ውሃ አቅርቦት እንዲሁም የገጠር መሬት ምዝገባን ዲጂታላይዝ የማድረግ ፕሮጀክት ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እየሠራች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
አምባሳደሯ አክለውም ከልማት ትብብር ባለፈ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ የቢዝነስ አጋርነት በመፍጠር ከኢትዮጵያ ጋር ያለንን ዲፕሎማሲያዊ ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ ነን ብለዋል።