በወለጋ ዞኖች እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች ለአካባቢው ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ትልቅ እድል ይፈጥራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በወለጋ ዞኖች እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች ለአካባቢው ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ትልቅ እድል ይፈጥራሉ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2018(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞኖች እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች ለአካባቢው ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ትልቅ እድል ይዘው የመጡ መሆናቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በምዕራብ፣ በቄለምና በምስራቅ ወለጋ ዞኖች የተለያዩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን የጎበኙ ሲሆን ከፊሎቹንም አስመርቀው ስራ ማስጀመራቸው ይታወሳል።
በኦሮሚያ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ስድስት ወራት ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት 33 ቢሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል
ከፕሮጀክቶቹ የመስኖ ግድብ፣ የከሰል ድንጋይ ማምረቻ ፋብሪካ፣ የወርቅ ማምረቻ፣ የበቆሎ ዱቄት መፍጫ ፋብሪካ፣ ኮሪደር ልማቶችና ሌሎች የልማት ስራዎች ይጠቀሳሉ።
ነዋሪዎቹ ወደ ስራ የገቡ ፕሮጀክቶች የዓመታት የልማት ጥያቄዎቻቸውን በአግባቡ የሚመልሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል የሌቃ ዋዩ አባ ገዳ ተስፋ ዲልጋሳ እንደተናገሩት፣ የተመረቁ ፕሮጀክቶች የአካባቢውን ህዝብ የልማት ጥያቄ ከመመለስ ባለፈ ተጠቃሚነትን የሚያሳድጉ ናቸው።
በልማት ፕሮጀክቶቹ ግንባታ ሂደትም በርካታ የአካባቢው ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው የልማት ስራው ትልቅ ተስፋ እና መነቃቃትን የፈጠሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በተጨማሪም እየተከናወን የሚገኘው የኮሪደር ልማት ከተሞችን በማስዋብ ለኑሮ ምቹና ተስማሚ በማድረግ የንግድ እንቅስቃሴን እያነቃቃ መሆኑን አንስተዋል።
በምስራቅ ወላጋ ዞን ጊዳ ወረዳ ነዋሪዋ ወይዘሮ ማርታ አብዲሳ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቶቹ ከዚህ በፊት ስንጠይቅ የነበረውን የልማት ጥያቄዎች የሚመልሱ በመሆናቸው ተደስተናል ብለዋል።
የልማት ስራዎቹ ለአገልግሎት መብቃት ለአካባቢው ወጣቶች ትልቅ ተስፋ የሚሰጡ መሆናቸውንም አክለዋል።
የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ተሊላ ተረፋ እንደተናገሩት፤ ከዚህ በፊት የተጓተቱ የነበሩ የልማት ፕሮጀክቶች መንግስትና ህዝብ ተቀናጅተው በመስራታቸው ለውጤት መብቃታቸውን አስረድተዋል።
ፕሮጀክቶቹ ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የስራ እድል ከመፍጠርም ባለፈ የመብራት፣ ውሃ፣ የመንገድ ልማትና የጤና ተቋማት ማስፋፈያ ስራዎች ለህብረተሰቡ ትልቅ ጥቅም የሚሰጡ ናቸው ብለዋል።