ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ስድስት ወራት ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት 33 ቢሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ስድስት ወራት ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት 33 ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን የክልሉ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ አስታወቀ።

ክልሉ በተያዘው ዓመት ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት 58 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ዕቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑም ተመላክቷል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ብርሃኑ በቀለ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በክልሉ ከተሞች ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት የሚገኝ ገቢ አሰባሰብ ሂደትን በማዘመንና ቀልጣፋ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ይገኝ የነበረው ገቢ ከ6 ቢሊዮን ብር ያልበለጠ እንደነበር አስታውሰው፣ ከለውጡ ዓመታት ወዲህ በከተሞች ያሉ አቅሞችን በጥናት በመለየትና ገቢን አሟጦ ለመሰብሰብ በመቻሉ የገቢ ዕድገት መታየቱን ተናግረዋል።

በ2017 በጀት ዓመት 37 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰበሰብ መቻሉን ያነሱት አቶ ብርሃኑ፤ በተያዘው ዓመትም 58 ቢሊዮን ብር ለመሰበሰብ እንደታቀደና ባለፉት ስድስት ወራትም ከአገልግሎቱ 33 ቢሊዮን ብር መገኘቱን ገልፀዋል።

በተለይም በመደመር እሳቤ መሰረት አመራሩ፣ ባለሙያውና ህዝቡ በመቀራረብና በመናበብ፣ የጊዜ አጠቃቀምን በማሻሻል፣ ውስን ካፒታልን በአግባቡ በመጠቀምና የተዘረጉ አቅጣጫዎችን ተግባራዊ በማድረግ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

የከተሞቹን የመሬት ካዳስተር ዲጂታላይዝ በማድረግ የተሻለ ለውጥ የተመዘገበ ሲሆን አዳማና ቢሾፍቱ ከተሞችን እንደማሳያ ጠቅሰው በሌሎች ከተሞችም ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስረድተዋል።

በዚሁ መሰረት የነዋሪዎችን የመሰረተ ልማት ፍላጎት ለማሟላትና ተደራሽ ለማድረግ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በየደረጃው ያለው አመራርንና ባለሙያ ርብርብ እያደረገ ነው ብለዋል።

የመንገድ ማስፋትና ወደ አስፋልት የመቀየር ስራ በሰፊው መሰራቱን አንስተው የአስፋልት፣ የጠጠር፣ የውስጥ ለውስጥ፣ የአደባባዮችና የእግረኛ፣ የሳይክል መንገዶችን በቅንጅት በመስራት ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

በክልሉ አሁንም ካለው ሀብትና አቅም አንጻር የገቢ አሰባሰቡ ላይ ቀሪ ስራዎች ያሉ መሆኑን አንስተው፣ ጥናትን መሰረት ባደረጉ ተግባራት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም