ቀጥታ፡

በእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት ከፍተኛ ለውጥ እየተመዘገበ ነው-ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፤የካቲት 18 /2018 (ኢዜአ)፡-ባለፉት ጥቂት ዓመታት አዳዲስ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ተግባራዊ በማድረግ በእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት ከፍተኛ ለውጥ መመዝገቡን ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

ግብርና ሚኒስቴር ቅንጅታዊና ተቋማዊ አሰራርን ለማጠናከር፣ ሀገር አቀፍ የእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ኤክስቴንሽን ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።


 

በዚሁ ወቅት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት አዳዲስ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ተግባራዊ በማድረግ በሀገሪቱ የእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ተመዝግቧል። 

ቀደም ሲል በስትራቴጂ ደረጃ ተዘንግቶ የቆየው ይህ ዘርፍ፣ አሁን ራሱን ችሎ እንዲደራጅና ልዩ የመንግስት ትኩረት እንዲሰጠው በመደረጉ አመርቂ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑ ገልጸዋል።

የእንስሳት እና ዓሣ ኤክስቴንሽን መተግበር ከጀመረ ወዲህ ለአርሶና አርብቶ አደሩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና እውቀቶችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።

በዚህም በእንስሳት ጤና አጠባበቅና በምርታማነት ላይ ተጨባጭ ለውጥ መጥቷል ብለዋል።

የእንስሳት በሽታ የዘርፉ ዋነኛ ተግዳሮት ሆኖ መቆየቱን ጠቁመው በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሮች በባለሙያ የታገዘ በሽታን መከላከያ ዘዴዎችን በመጠቀማቸው ውጤታማ እየሆኑ መጥተዋል ብለዋል።

ምንም እንኳን እስካሁን የተከናወኑ ስራዎች ተስፋ ሰጭ ቢሆኑም፣ አሁንም በዝርያ ማሻሻያና በዘመናዊ የእንስሳት ጤና አጠባበቅ ረገድ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት የሁሉም አካላት ተሳትፎ መጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል።

መንግስት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በነደፋቸው የተለያዩ ኢኒሼቲቮች አማካይነት፣ ኢትዮጵያ ካላት እምቅ የእንስሳት ሀብት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።


 

የሲዳማ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አሰፋ ፎና በበኩላቸው በእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት በክልሉ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የእንስሳትን ዝርያ ማሻሻል ላይ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 


 

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ዘርፍ ኃላፊ ታመነ በቀለ በበኩላቸው የእንስሳት ምርትና ምርታማነት ለማሻሻል ዘመናዊ የእንስሳት መኖ ልማት መጀመሩን ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ እንስሳት ሐኪሞች ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ ፕሮፌሰር እንድሪያስ ዘውዱ የእንስሳት ጤና ኤክስቴንሽን ለዘርፉ ዕድገት ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸው፥ ማህበሩ በእንስሳት ጤና ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም