7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ እየሰራን ነው - የፖለቲካ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ እየሰራን ነው - የፖለቲካ ፓርቲዎች
ቦንጋ፤ የካቲት 19/2018(ኢዜአ)፦ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ቅቡልነት ያለው ሆኖ በኢትዮጵያ አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ እየሰሩ እንደሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፁ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በመጪው ግንቦት ወር ለማካሄድ ቀነ ቀጠሮ መያዙ ይታወቃል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ግንባታ ሀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል
ለምርጫው እያደረጉ ያሉትን ዝግጅት በተመለከተ ኢዜአ ካነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ፓርቲ የካፋ ዞን ሰብሳቢ አክሊሉ አለማየሁ፣ በዘንድሮ ምርጫ በተሻለ መልኩ ጠንካራ ተወዳዳሪ ሆነው ለመቅረብ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ምርጫው በሀሳብ የበላይነት ላይ ብቻ የተመሰረተ እንዲሆን ምቹ ምህዳር መፈጠሩን ጠቁመው ይህን በመጠቀም ምርጫው ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ ተዓማኒና ቅቡልነት ኖሮት በኢትዮጵያ አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ ፓርቲያቸው መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
የእናት ፓርቲ የካፋ ዞን ሰብሳቢ መምህር እስራኤል ጌታቸው ፓርቲያቸው ለጠቅላላ ምርጫው በቂ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
እጩዎቻቸውን ማስመዝገባቸውንና ለህዝብና ለሀገር ሰላም ቅድሚያ በመስጠት በሀሳብ የበላይነት ላይ የተመሠረተ ሰላማዊ ውድድር ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢና ሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት ፓርቲ አባል የሆነው ካፋ አረንጓዴ ፓርቲ ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ በበኩላቸው፣ የዘንድሮ ምርጫ የተሻለ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየሰራን ነው ብለዋል።
ምርጫ የሀገረ መንግስት ግንባታን ጨምሮ ቀጣይ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎችን የሚወስን በመሆኑ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በሀሳብ ልእልና ላይ የተመሰረተ ውድድር ማድረግ እንደሚገባም ነው አቶ ሰለሞን የተናገሩት።
ለምርጫው ስነ-ምህዳር መስፋትና አስቻይ ሁኔታ መፈጠር የመንግስት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የህዝቡና የሌሎች ተዋናዮች ሚና የጎላ መሆኑንም አንስተዋል።
ከዚህ አንጻር ፓርቲያቸው የካፋ አረንጓዴ ፓርቲ ለእጩዎችና ለአባላት የምርጫ ህግን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ ግንዛቤ ፈጥሮ እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
እጩዎቹን ማስመዝገብ፣ የምርጫ ምልክቱንና ፕሮግራሙን የማስተዋወቅ እንዲሁም ሌሎች ዝግጅቶችን ማድረጉን ጠቅሰው፣ ፖሊሲውንና ማኔፌስቶውን እስከታች የማስረፅ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።