የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ግንባታ ሀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ግንባታ ሀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል
ባህር ዳር፤ የካቲት 19/2018(ኢዜአ)፦ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀሳብ የበላይነትና በመከባበር ላይ የተመሰረተ የምርጫ ቅስቀሳና ክርክር በማድረግ ለሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ግንባታ ሀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች አመለከቱ።
በኢትዮጵያ በመጪው ግንቦት ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ ሀሳቦቻቸውን በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በመጠቀም ማስተዋወቅና የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ ጀምረዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች መጪው ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ያላቸውን ፍላጎት ገልጸው ለተግባራዊነቱም በተለይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ብዙ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡት የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወርቅነህ እንዳለው፣ ምርጫ ህዝቡ በመረጠው አካል የሚተዳደርበትና የስልጣን ሉዓላዊነት የሚረጋገጥበት የዴሞክራሲ ሥርዓት መሆኑን ገልጸዋል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀሳብ የበላይነትና በመከባበር ላይ የተመሰረተ የምርጫ ቅስቀሳና ክርክር በማድረግ ስልጡን የፖለቲካ ባህል ሊከተሉ ይገባል ብለዋል።
ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳቸውን ሕግና ሥርዓትን ባከበረ መንገድ ማካሄድና ለህዝብ የሚጠቅም አማራጭ ሀሳብ ማምጣት አለባቸው ሲሉም አክለዋል።
ያለምወርቅ ደበላና የሱፍ ማስረሻ የተባሉ ነዋሪዎች በበኩላቸው በምርጫ ቅስቀሳና ክርክር መድረኮች ወቅት ፓርቲዎች አማራጭ ሀሳባቸውን በማቅረብ ላይ ብቻ ማተኮር እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ሀገርን ሊጎዱ የሚችሉና ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ አካሄዶችን ከመከተል መቆጠብ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።
የምርጫው ሂደት በሰለጠነና ዘመኑን በሚመጥን መንገድ መከናወን እንደሚገባ ጠቅሰው፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነ-ምግባርን ተከትለው ቅስቀሳ ሊያደርጉ ይገባል ነው ያሉት።