ቀጥታ፡

የሰውሰራሽ አስተውሎት ትምህርትን ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ መስጠት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2018(ኢዜአ)፦ የሰውሰራሽ አስተውሎትና የዲጂታል ክህሎት ማሳደጊያ ትምህርትን ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ መስጠት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር ገለፀ።

በትምህርት ሚኒስቴር የኢ-ለርኒንግና የ5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ አስተባባሪ ሙሉነህ አጥናፉ ለኢዜአ እንዳሉት፥ በሀገሪቱ እየተተገበሩ ያሉ የሪፎርም ስራዎችን ለማሳለጥና ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ትግበራ ውጤታማነት የሰው ኃይል ልማት ወሳኝ ነው።  

የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ የወጣቱን የዲጂታል፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ አቅም ማጎልበት ወሳኝ ነው

ለዚህም የዲጂታል ክህሎትና እውቀትን ማበልፀግ እንደሚያስፈልግ አንስተው ሚኒስቴሩ ሀገራዊ የሪፎርም አጀንዳዎችንና ተልዕኮውን መሰረት ያደረገ ጉዞ መጀመሩን ተናግረዋል።

የመምህራንና ተማሪዎችን እንዲሁም የህብረተሰቡን የዲጂታል እውቀትና ክህሎት ማሳደጊያ መርኃ ግብሮችን ለመተግበር እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ የሆነው የሰውሰራሽ አስተውሎት መሆኑን አንስተው ዘርፉ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን ጠቀሜታ ማረጋገጥ የሚያስችል ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የሰውሰራሽ አስተውሎትና የዲጂታል ግንዛቤን የሚያሳድግ ትምህርት ከአንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ በስርዓተ ትምህርት ውስጥ በማካተት ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ መምህራንና ተማሪዎችን የዲጂታል ክህሎትና እውቀት ማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ለዚህም የ5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ስልጠና እንዲወስዱ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጨምረው አስረድተዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር ከዲጂታሉ ዓለም ጋር ብቁና ተወዳዳሪ ሆነው የሚራመዱ ታዳጊዎችንና ወጣቶችን ለማፍራት የዲጂታል እውቀትና ክህሎት መሠረቶች ላይ ትኩረት መስጠቱንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም