ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ የወጣቱን የዲጂታል፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ አቅም ማጎልበት ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ የወጣቱን የዲጂታል፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ አቅም ማጎልበት ወሳኝ መሆኑን የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢዲ ኮኔክት ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የ2026 የኢትዮ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ሳይንስ እና የትምህርት ፌስቲቫል ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።


 

ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ መድረክ የመክፈቻ መርሐ ግብር ላይ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮችና ተማሪዎች ተገኝተዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፤ በዲጂታል ዓለም ተወዳዳሪ ለመሆን ወጣቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ለሀገሪቱ የዲጂታላይዜሽን ጉዞ መሠረት መሆኑን ጠቁመው ፌስቲቫሉ ወጣቶች በትምህርት ልቀውና በሳይንስ መሪ መሆን እንዲችሉ ዓለም አቀፍ ልምድ ካላቸው ተቋማት ጋር ምህዳር እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን የወጣቶችን የፈጠራ ስራ የሚያጎለብት "የሰመር ካምፕ" ለማዘጋጀት ማቀዱን ይፋ አድርገዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሽኔ በበኩላቸው፣ የሀገርን ብልፅግና ለማረጋገጥ በሰው ሀብት ልማት ላይ መስራት ቀዳሚ ተግባር ነው ብለዋል፡፡


 

ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ሥራዎች እንደ አማራጭ የሚታዩ ሳይሆን ለዘመናዊ ስልጣኔ መሰረት የሆኑ የልማት ምሰሶዎች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

የአፍሪካ ህብረት የጤና፣ ሰብአዊ መብቶች እና ማህበራዊ ልማት ኮሚሽነር አምባሳደር ሚንአታ ሳማቴ ሴሱማ፣ የወጣቶች ተሳትፎ ለአጀንዳ 2063 ስኬት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የዩኔስኮ የሰላም ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ጋይ ጆከን በበኩላቸው አፍሪካ ያላትን የወጣት ኃይል ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ እንደ ትልቅ ስትራቴጂካዊ ሀብት ሊወሰድ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢድ ኮኔክት ኢትዮጵያ መስራች ኢንጂነር ሳሙኤል ንጉሴ እንዳሉትም፤ ተቋማቸው ተማሪዎችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ ይሰራል፡፡

በፌስቲቫሉ ላይ የታደሙት ተማሪ ካይረን ግርማ እና ሲፈን ዮሃንስ በበኩላቸው፣ መድረኩ የትምህርት ዕድሎችን ለማግኘትና ዓለም አቀፍ እውቀትን ለመቅሰም ትልቅ በር እንደከፈተላቸው መስክረዋል።

ፌስቲቫሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ የተደረገውን የዲጂታል 2030 ስትራቴጂ ግቦች ከማሳካት አንጻር ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለውም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም