ቀጥታ፡

በዞኑ ሴቶች በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር  ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ ነው

አምቦ፤ የካቲት 19/2018 (ኢዜአ)፡- በምዕራብ ሸዋ ዞን በሌማት ትሩፋት  መርሃ ግብር የተሳተፉ ሴቶች በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ፍጆታቸውን ከመሸፈን ባለፈ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መሆናቸውን   ገለጹ።

ከመርሐ ግብሩ ተጠቃሚዎች መካከል በኤጀሬ ወረዳ በዶሮ እርባታ ሥራ የተሰማሩት ወይዘሮ መስቱ ካሳሁን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ 10 ሴቶች ሆነው በማህበር ተደራጅተው ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል። 

የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ዜጎችን ከተረጂነት ወደ አምራችነት እያሸጋገረ ነው

በመጀመሪያ 1 ሺህ 300 የሥጋና የእንቁላል ጣይ ዶሮዎችን በማርባት የጀመሩ ሲሆን፣ አሁን ላይ የዶሮዎቹን ብዛት ወደ 3 ሺህ 800 በማድረስ ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

ወይዘሮ መስቱ አክለውም በአሁኑ ወቅት በቀን 700 እንቁላሎችን እያገኙ መሆኑን የገለጹ ሲሆን ምርታቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ ለአካባቢው ገበያ እያቀረቡም ነው።

ከሽያጩ በሚያገኙት ገቢ ቤተሰባቸውን በጥሩ ሁኔታ እያስተዳደሩና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውንም እያሳደጉ መሆኑን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በወተት ላሞች እርባታ የተሰማሩት ወይዘሮ ባይሴ ቱሉ፣ ቀደም ሲል በቀን ሥራ ይተዳደሩ እንደነበር  አስታውሰዋል። 


 

የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ከተጀመረ ወዲህ ግን፣ በቀን ከአንድ ላም በአማካይ 10 ሊትር ወተት ለገበያ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።

የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ ዕለታዊ ገቢያቸውን ማሳደግ መቻላቸውን ገልጸው ለዚህ ስኬት የወረዳው ሴቶች እና ህጻናት ጉዳይ ጽሕፈት ቤት እና የሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ጽሕፈት ቤት የሰጧቸው ሥልጠና ትልቅ እገዛ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

የኤጀሬ ወረዳ ሴቶች እና ህጻናት ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሃና ኃይለማርያም ፤ በበጀት ዓመቱ ለ1 ሺህ 15 ሴቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ እንደነበረ ገልጸዋል።


 

በተከናወኑ የተቀናጁ ሥራዎች 1 ሺህ 600 ሴቶችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው ሴቶቹ በከብት ማድለብ፣ በዶሮ እርባታ፣ በወተት ላም እርባታና በሌሎችም የሥራ ዘርፎች መሰማራታቸውን አስረድተዋል።

የምዕራብ ሸዋ ዞን የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ክብቱ ድሪባ በበኩላቸው፣ በዞኑ የሴቶችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የግብርናና ሌሎች ኢኒሼቲቮች ውጤት እያመጡ መሆኑን ገልጸዋል።


 

እንደ ኃላፊዋ ማብራሪያ፣ በበጀት ዓመቱ ለ20 ሺህ ሴቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ፣ እስካሁን ለ19 ሺህ 250 ሴቶች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል።

ሴቶች የቤተሰባቸውን የምግብ ፍጆታ ከመሸፈን ባለፈ ምርታቸውን ለገበያ በማቅረብ ለሌሎች አርሶ አደሮች አርአያ እየሆኑ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም