የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ዜጎችን ከተረጂነት ወደ አምራችነት እያሸጋገረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ዜጎችን ከተረጂነት ወደ አምራችነት እያሸጋገረ ነው
አዳማ ፤ የካቲት 17/2018(ኢዜአ)፦ በከተሞች እየተተገበረ የሚገኘው የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን ከተረጂነት ወደ አምራችነት በማሸጋገር ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ገለፀ።
ለ3ኛው ዙር ልማታዊ ሴፍቲኔት ስራ 250 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ የፋይናንስ ድጋፍ መገኘቱም ተገልጿል።
የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት እና ስራ ፕሮጀክት የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ አመት አፈጸጸም ግምገማ እና የ3ኛው ዙር ተጨማሪ ፋይናንስ ድጋፍ ማብሰሪያ መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ደጀን እንዳስታወቁት፤ የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት በ88 ከተሞች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ አድርጓል።
የፕሮግራሙ ዓላማ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ጊዜያዊ ድጋፍ በማድረግ ማቆየት ብቻ ሳይሆን በየሶስት ዓመቱ በማስመረቅ ዜጎች ከተረጂነት ተላቀው ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ መሆኑን ገልፀዋል።
ፕሮግራሙ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች ጥሪት በማፍራት ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡ አስችሏል
በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም በርካታ ዜጎች ከተረጂነት ወደ አምራችነት የተሸጋገሩ ሲሆን በተያዘው በጀት ዓመትም 879 ሺህ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎችን የመደገፍ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ እስካሁን ባለው ትግበራ ዜጎችን ከድህነት በማላቀቅ ሀብት እና ጥሪት እንዲያፈሩ በማስቻል ውጤታማ መሆኑን አስረድተዋል።
ለ3ኛው ዙር ልማታዊ ሴፍትኔት ስራ 250 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ የፋይናንስ ድጋፍ የተገኘ በመሆኑ 318 ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት እና ሥራ ፕሮጀክት አስተባባሪ ኢንጂነር አንዷለም ገሰሰ እንዳሉት፤ መንግስት ተግባራዊ ካደረጋቸው ሰው ተኮር የልማት ተግባራት መካከል የልማታዊ ሴፍቲኔት እና ሥራ ፕሮጀክት አንዱ ነው።
ፕሮጀክቱ እንደ ሀገር ከተጀመረ ወዲህ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ በማግኘት በሁሉም ክልሎች ውጤታማ ተግባራት ማከናወን የተቻለበት መሆኑንም ገልፀዋል።
በዚህም 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎችን መሠረት ያደረጉ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው ይህም በርካታ ዜጎችን ከዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ወደ አምራችነት ማሸጋገር ማስቻሉን ገልጸዋል።
በሶስተኛው ዙርም 16 ተጨማሪ ከተሞች በፕሮጀክቱ እንደሚታቀፉ ገልጸው በተለይ ለ100 ሺህ ወጣቶች በፕሮጀክቱ የሥራ እድል ለማመቻቸት ይሰራል ብለዋል።
በተጨማሪም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት 8 ሺህ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ካሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ በማንሳትና በመደገፍ ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል ተግባርም እንደሚከናወን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት በሰጠችው ልዩ ትኩረት እና ለተመዘገቡ ስኬቶች ዓለም ባንክ እና ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እውቅና እንደተሰጣትም ነው የተናገሩት።
ፕሮጀክቱ በፌዴራል መንግስትና በዓለም ባንክ ድጋፍ የሚተገበር መሆኑ ይታወቃል።