የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የቀጣይ ስምንት ወራት ዐበይት የትኩረት ጉዳዮች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የቀጣይ ስምንት ወራት ዐበይት የትኩረት ጉዳዮች
የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የካቲት 11 ቀን 2018 ዓ.ም በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን የአራት ዓመታት የስራ አፈፃፀም በማዳመጥና ያልተከናወኑ ተግባራትን ከግምት በማስገባት የኮሚሽኑን የስራ ዘመን ለስምንት ወራት ማራዘሙ የሚታወስ ነው፡፡
በዚህ መሰረት ኮሚሽኑ ኃላፊነቱን እንዲወጣ በተጨማሪነት በተሰጠው የስምንት ወራት ጊዜ ውስጥ የሚከተሉትን ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ያከናውናል፡፡
የትግራይ ክልልን የምክክር ሂደት ማካሄድ፤
በተለያየ መልኩ የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን ለኮሚሽኑ ምክር ቤት በማቅረብ፣ በየፈርጁ ለይቶ በማዘጋጀት፣ በመቅረጽ የምክክር አጀንዳዎችን ለሕዝብ ይፋ ማድረግ፤
የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ አወያዮች እና አመቻቾችን መለየት፣ ማሰልጠን እና ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ዝግጁ እንዲሆኑ ማድረግ፤
አሳታፊና አካታች የሆነ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤን ማካሄድ፤
ከሀገራዊ ምክክሩ የሚገኙ ምክረ ሀሳቦች ማጠናቀር፣ ምክረ ሀሳብ ማዘጋጀትና ተግባራዊነታቸውን መከታተል፤
ሀገር አቀፍ ንቅናቄ በማድረግ የግንዛቤ ስራዎችን ማስፋትና የነቃ ተሳትፎ እንዲኖር ማድረግ፤
የዶክመንቴሽን ስራዎችን ዲጂታላይዝድ ማድረግና ተደራሽነቱን ማስፋት ናቸው፡፡
በመሆኑም ኮሚሽኑ ባለፉት አራት ዓመታት ባከናወናቸው ተግባራት እንደ አስፈላጊነቱ እና ድጋፍን በጠየቀ ሰዓት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን እያመሰገነ በመጪው ስምንት ወራት በሚያከናውናቸው ተግባራትም መሰል ተነሳሽነቶችና ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ባለሙሉ እምነት መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡