ፋይዳ መታወቂያን ከተለያዩ አገልግሎቶች ጋር ማስተሳሰር ከተጀመረ ወዲህ የተመዝጋቢዎች ቁጥር እየጨመረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ፋይዳ መታወቂያን ከተለያዩ አገልግሎቶች ጋር ማስተሳሰር ከተጀመረ ወዲህ የተመዝጋቢዎች ቁጥር እየጨመረ ነው
አሶሳ፤ የካቲት 19/2018(ኢዜአ)፦ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን ከተለያዩ አገልግሎቶች ጋር ማስተሳሰር ከተጀመረ ወዲህ የተመዝጋቢዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የምዝገባ አስተባባሪ ደጀኔ ገብሬ አስታወቁ።
በ2014 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተጀመረው የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተለያዩ አገልግሎቶች ጋር በማስተሳሰር የዲጂታል መሠረተ ልማትን ለማሳለጥ እየተሰራ ይገኛል።
በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከ160 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ደምበኞች የተቀላጠፈ አገልግሎት ተሰጥቷል
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የምዝገባ አስተባባሪ ደጀኔ ገብሬ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ አካታች እንዲሆን ከተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በቅንጅት እንዲሰራ ተደርጓል።
በዚህም የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተመዝጋቢዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ገልፀው፤ የምዝገባ ፕሮግራሙ ከተጀመረ ወዲህ 36 ሚሊዮን ዜጎች ተመዝግበው የመታወቂያው ባለቤት መሆናቸውን ገልጸዋል።
ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የአገልግሎት አሰጣጥን የሚያቀላጥፍ እና ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ዓይነተኛ ሚና እያበረከተ እንደሆነ ጠቁመው፤ በተለይም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ከግብ ለማድረስ ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።
ለአብነትም ፋይዳን ከአርሶ አደሩ የመሬት ባለቤትነት ጋር ማስተሳሰር በርካታ ዜጎች እንዲመዘገቡ ከማድረግ ባለፈ አርሶ አደሩ ይዞታውን አስይዞ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኝ እና ማሳውን በአግባቡ ለማስተዳደር እንደሚያግዘው አንስተዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እስካሁን ከ250 ሺህ በላይ ዜጎች የተመዘገቡ ሲሆን አፈጻጸሙን ለማሻሻል የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚያስፈልግም አስተባባሪው አስታውቀዋል።
በክልሉ የመቶ ፐርሰንት ግብ አፈጻጸም ዝቅተኛ በመሆኑ ከተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በማስተሳሰር ዕቅዱን ማሳካት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሬትና ህብረት ስራ ማደራጃ ቢሮ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር "ብሔራዊ መታወቂያ ለገጠር መሬት ባለይዞታዎች" በሚል መሪ ሃሳብ የምክክር መድረክ መካሄዱ ይታወሳል።