ቀጥታ፡

በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከ160 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ደምበኞች የተቀላጠፈ አገልግሎት ተሰጥቷል

አዲስ አበባ፤የካቲት 12/2018 (ኢዜአ)፡-የመሶብ አገልግሎት ከተጀመረ ወዲህ ከ160 ሺህ በላይ ለሆኑ ደምበኞች የተቀላጠፈ አገልግሎት መሰጠቱን የፌዴራል መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አንተነህ ማሞ ገለጹ።

ኢትዮጵያን በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ቅልጥፍናን በማፋጠን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚጠቀሱ 50 ሀገራት መካከል አንዷ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሚያዝያ 18/2017 ዓ.ም የመንግስትን አገልግሎት ጥራትና ቅልጥፋና የሚያዘምን የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ሥራ ማስጀመራቸው ይታወሳል።

በማዕከሉም ቅሬታ የሚበዛባቸውን የመንግስት አገልግሎቶች በመለየት ዜጎች በአንድ ማዕከል አገልግሎት (ዋን ስቶፕ ሰርቪስ) ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ ቀልጣፋ አገልግሎት የሚያገኙበትን ዕድል ፈጥሯል።

የፌዴራል መሶብ የአንድ ማዕከል ዳይሬክተር ጄኔራል አንተነህ ማሞ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ዘመናዊና ቀልጣፋ የመንግስት አገልግሎት ምኅዳር በመፍጠር የተገልጋዮችን እርካታ ማረጋገጥ ያስቻለ ስኬት ተገኝቷል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነት የተጀመረው የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትም የዜጎችን የመልካም አስተዳደር ችግር በመቅረፍ እመርታዊ ውጤት ማስገኘቱን ገልጸዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ከተጀመረ ወዲህ ባሉት አሥር ወራት ብቻ ከ160 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተገልጋዮች ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት መሰጠቱን አስታውቀዋል።

በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የሚሰጡ የመንግስት አገልግሎቶችም ዜጋ ተኮር፣ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍልና የተገልጋዮችን ፍላጎት ማዕከል ያደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በዲጂታላይዜሽን ሥርዓት የተዋቀሩት የመሶብ አንድ ማዕከል ሁሉም አገልግሎቶች ዜጎች ዘመናዊና ጥራት ያለው ቀልጣፋ የመንግስት አገልግሎት እንዲያገኙ እያስቻለ ነው ብለዋል።

በዲጂታል 2030 የአገልግሎት አሰጣጥ አመላካች ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚጠቀሱ 50 አገራት መካከል አንዷ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በኦን ላይን በየትኛውም ቦታ ሁሉንም አገልግሎቶች እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በመሶብ የአንድ ማዕከል የሚገቡ ተቋማትም አስፈላጊ መረጃዎችን ከሌሎች ተቋማት ጋር ተሰናስለው የሚሰጡበት ሥርዓት መፈጠሩም የመረጃ ልውውጥ ፖሊሲ ላይ ወሳኙ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።

በፌዴራል የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በ12 ተቋማትና በ41 አገልግሎቶች ተግባራዊ ማድረግ የተጀመረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም ተቋማትን ወደ 23 በማሳደግ አጠቃላይ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ወደ 187 ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም