ቀጥታ፡

በመስኖ ካለማነው በርበሬና የጓሮ አትክልት ልማት ተጠቃሚ ሆነናል - አርሶ አደሮች

ሳውላ፤ የካቲት 19/2018 (ኢዜአ)፡- በጎፋ ዞን በመደበኛ መስኖ በርበሬና ሌሎች የጓሮ አትክልቶችን በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን አርሶ አደሮች ገለጹ።

በዞኑ ከ9 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሽንኩርት፣ በቃሪያ፣ በበርበሬና በሌሎች የጓሮ አትክልቶች መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል።

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ስራ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችንን እያሳደገው ነው

አርሶ አደሮቹ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በበጋ መስኖ የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን በማልማት ከሽያጩ ከ800 ሺህ እስከ 2 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት ችለዋል።

ወጣት አርሶ አደር ታሪኩ እርሳሴ፤ በዞኑ ኡባ ደብረ ፀሀይ ወረዳ የሸሌ ቡኔ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆን ላለፉት ስድስት ዓመታት በበጋ መስኖ ስራ ላይ መሰማራቱን ነው የገለፀው።


 

አርሶ አደሩ ባለው ሁለት ሄክታር ማሳ ላይ በርበሬ፣ ቲማቲም፣ ሽንኩርትና ሌሎች የጓሮ አትክልቶችን እያለማ ሲሆን በገበያ ላይ ያለውን ተፈላጊነት መሰረት አድርጎ የበርበሬና የሚጥሚጣ ምርት ላይ ማተኮሩን ይገልፃል።

ከሚጥሚጣ ምርት ብቻም 2 ሚሊዮን ብር ገቢ እያገኘ መሆኑን የገለፀው አርሶ አደር ታሪኩ ከራሱ አልፎ ለ30 ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ  የስራ ዕድል መፍጠሩንም ጠቁሟል።


 

ወጣት አሰበ አበራ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም በዲግሪ ተመርቆ ሲቪውን ይዞ ስራ ከማፈላለግ ይልቅ ያለውን ፀጋ በመመልከት ከአባቱ ጋር በመሆን ሽንኩርትና በርበሬ ልማት ላይ በመሰማራት የተሻለ ተጠቃሚ መሆን መቻሉን ይናገራል።


 

ወጣቱ አርሶ አደር በሩብ ሄክታር ማሳ ላይ ካለማው ሽንኩርትም 40 ሺህ ብር የተጣራ ገቢ እንዳገኘ ነው የሚገልፀው።

የኡባ ደብረ ጸሀይ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አገኘሁ ሲራጅ በበኩላቸው፤ በወረዳው ከ1 ሺህ 20 ሄክታር በላይ መሬት በጓሮ አትክልት እየለማ እንደሆነ ተናግረዋል።


 

በዋናነት ሽንኩርት፣ በርበሬ፣ ጥቅል ጎመንና ሀባብ በማምረት አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱንም አመልክተዋል።

በዞኑ በበጋ መስኖ ከ9 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የጓሮ አትክልቶች የተሸፈነ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የጎፋ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ደግፌ ናቸው።


 

በዋናነት በበርበሬና ሚጥሚጣ ልማት ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ነው የገለጹት።

እንደ ኃላፊው ገለፃ አንድ አርሶ አደር በስድስት ሄክታር ካለማው ሚጥሚጣ እስከ ሁለት ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት እንደቻለም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም