ቀጥታ፡

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ስራ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችንን እያሳደገው ነው

ሮቤ፣ የካቲት 17/2018(ኢዜአ)፡- የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ አልፎ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እያገዛቸው መሆኑን በባሌ ዞን የጋሰራ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።

በዞኑ በዘንድሮ የበጋ ወቅት በመስኖ ለማልማት ከታቀደው 183 ሺህ 500 ሄክታር መሬት 149 ሺህ ሄክታሩን ማልማት መቻሉም ተገልጿል።

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር የውሀ ሀብቶችን በማቀናጀት የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ግብ ተጥሎ እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል።

በልማቱም እንደ ክልል ብሎም እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማረጋገጥና የዜጎችን ሕይወት ትርጉም ባለው መልኩ ለማሻሻል በተሰሩት ሥራዎች ተጨባጭ ውጤቶች ታይተዋል።

የበጋ መስኖ የሥራ እንቅስቃሴን በማስመልከት አስተያየታቸውን የሰጡ በባሌ ዞን የጋሠራ ወረዳ አርሶ አደሮች እንዳሉት የተለያዩ የውኃ አማራጮችን በመጠቀም እያለሙ ከሚገኙት የበጋ መስኖ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እየተሻሻለ መጥቷል።

ከጋሠራ ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል አብዱረህማን ሰኢድ በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም የዝናብ ውኃን ብቻ ጠብቀው በሚያካሄዱት ልማት የልፋታቸውን ያህል ተጠቃሚ እንዳልነበሩ አስታውሰዋል።

ከሦስት ዓመታት ወዲህ ግን በግብርና ባለሙያዎች በተደረገላቸው ሙያዊ እገዛ በአካባቢያቸው የሚገኙ የውሃ አማራጮችን በሞተር ፓምፕ በመሳብ ስንዴን በበጋ ጭምር በማልማት ተጠቃሚ እያሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ የምርት ወቅት ከሌሎች የአካባቢያቸው አርሶ አደሮች ጋር በኩታ ገጠም በመደራጀት በአንድ ሄክታር ማሳቸው ላይ ያለሙት ስንዴ በጥሩ ቁመና ላይ መሆኑንና ከሄክታር እስከ 55 ኩንታል እንደሚጠብቁም ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የግብርና አሰራሮችን በመጠቀም እያለሙ ከሚገኙት የስንዴ ሰብል በሄክታር እስከ 65 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ የገለጹት ደግሞ ሌላው የልማቱ ተሳታፊ አርሶ አደር በከር አብዶ ናቸው።

መንግሥት ያደረገላቸው የሙያ ድጋፍና የሞተር ፓምፕ አቅርቦት በዘርፉ ውጤታማ እንዲሆኑ እየረዳቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የጋሠራ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርናና መሬት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተሾመ ተፈራ በበኩላቸው በወረዳው በበጋው መስኖ ወቅት ከ21 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ስንዴን እያለሙ ለሚገኙ አርሶ አደሮች የተለያዩ ድጋፎችና ማበረታቻዎች እየተደረጉ ነው ብለዋል።

በዞኑ ዘንድሮ በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ከታቀደው 183 ሺህ 500 ሄክታር መሬት እስካሁን ከ149 ሺህ ሄክታር የሚበልጠውን ማልማት መቻሉን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሙአዊያ ፉአድ ናቸው።

የበጋ መስኖ ስንዴን ውጤታማ ለማድረግ 2 ሺህ የሚሆኑ የውኃ መሳቢያ ሞተር ፓምፖች በረዥም ጊዜ ብድር በልማቱ ለተሳተፉ አርሶ አደሮች በተለያዩ ጊዜያት መሰራጨቱን ጠቅሰዋል።

በበጋው መስኖ ወቅት እየለማ ከሚገኘው አጠቃላይ ልማት ከ7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም