የሊጉ መሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከባህርዳር ከተማ ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
የሊጉ መሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከባህርዳር ከተማ ጋር ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የ15ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይደረጋሉ።
ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ባህርዳር ከተማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም ይጫወታሉ።
በፕሪሚየር ሊጉ ነገሌ አርሲ ከኢትዮጵያ ቡና ይጫወታሉ
ባህርዳር ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው 14 ጨዋታዎች ሶስቱን ሲያሸንፍ 10 ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይቷል።
በጨዋታዎቹ ላይ 8 ግቦችን ከመረብ ሲያሳርፍ 17 ጎሎችን አስተናግዷል። ባህርዳር ከተማ በ10 ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በውድድር ዓመቱ 14 ጨዋታዎችን አድርጎ 12 ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። 32 ግቦችን ሲያስቆጥር ሰባት ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ቡድኑ በ37 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ካሸነፈ የሊጉን መሪነት ያጠናክራል። ከተከታዩ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት ከፍ ያደርጋል።
ባህር ዳር ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።
በሌላኛው መርሐ-ግብር አዲስ አበባ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
አዲስ አበባ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች መካከል ሁለቱን ሲያሸንፍ 10 ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።
በጨዋታዎቹ ሰባት ግቦችን ሲያስቆጥር 27 ግቦችን አስተናግዷል። አዲስ አበባ ከተማ በስምንት ነጥብ 14ተኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ እስከ አሁን ካከናወናቸው 14 ጨዋታዎች መካከል አምስቱን ሲያሸንፍ ስምንት ጊዜ ሽንፈት ቀምሷል። በአንድ ጨዋታ ደግሞ ነጥብ ጥሏል። 13 ግቦችን ሲያስቆጥር 21 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ድሬዳዋ ከተማ በ16 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል።
ሁለቱም ቡድኖች በሊጉ ተከታታይ ድላቸውን ለማስመዝገብ ይጫወታሉ።