በፕሪሚየር ሊጉ ነገሌ አርሲ ከኢትዮጵያ ቡና ይጫወታሉ - ኢዜአ አማርኛ
በፕሪሚየር ሊጉ ነገሌ አርሲ ከኢትዮጵያ ቡና ይጫወታሉ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2018 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ21ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ምሽት 12 ሰዓት ላይ ነገሌ አርሲ ከኢትዮጵያ ቡና በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
የሊጉ መሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከባህርዳር ከተማ ጋር ይጫወታል
ነገሌ አርሲ በሊጉ ባደረጋቸው 20 ጨዋታዎች በ10ሩ አሸንፎ በአራቱ ተሸንፎ በቀሪ ስድስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 22 ግቦችን ሲያስቆጥር 13 ጎሎችን አስተናግዷል።
አዲስ አዳጊው ነገሌ አርሲ በ36 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና እስከ አሁን በውድድር ዓመቱ ካከናወናቸው 19 ጨዋታዎች መካከል ስድስቱን ሲያሸንፍ በስምንቱ ሽንፈት አስተናግዷል። አምስት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።
16 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 20 ጎሎች ተቆጥረውበታል። ቡናማዎቹ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀራቸው በ23 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
በ20ኛ ሳምንት ከአርባምንጭ ከተማ ጋር አንድ አቻ የተለያየው ነገሌ አርሲ ወደ አሸናፊነት ይመለሳል።
ነገሌ አርሲ ካሸነፈ የሊጉን መሪነት ከሲዳማ ቡና በጊዜያዊነት ይረከባል።
በሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታውን የሚያደርገው ኢትዮጵያ ቡና በድል ጉዞውን ለመጀመር ይጫወታል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር በሁለተኛ ሳምንት ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 2 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
በሌላኛው መርሐ-ግብር አዳማ ከተማ ከሸገር ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
አዳማ ከተማ በ31 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። አዲስ አዳጊው ሸገር ከተማ በ22 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ጨዋታው አዳማ ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ፣ ሸገር ከተማ ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።
መቻል ከመቀሌ 70 እንደርታ ምሽት 12 ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
መቻል በ30 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። መቀሌ 70 እንደርታ በ21 ነጥብ 17ኛ ደረጃ ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ያላሸነፈው መቻል ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ይጫወታል።
መቀሌ 70 እንደርታ ካሸነፈ ተከታታይ ድሉን ያስመዘግባል።
ከቀኑ 9 ሰዓት ድሬዳዋ ከተማ ከወላይታ ድቻ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ድሬዳዋ ከተማ በ25 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል። ወላይታ ድቻ በ19 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች አቻ የወጣው ድሬዳዋ ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።
ወላይታ ድቻ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ጨዋታውን ያደርጋል።