ቀጥታ፡

ሪያል ማድሪድ ፒኤስጂ እና ጋላታሳራይ ጥሎ ማለፉን ተቀላቀሉ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2018 (ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ማጣሪያ ሶስት የመልስ ጨዋታዎች ተደርገዋል።

አትላንታ ወደ ጥሎ ማለፍ ገብቷል

ሪያል ማድሪድ ቤኔፊካን 2 ለ 1 አሸንፏል።



በበርናባው ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ኦሪሊየን ቹአሜኒ እና ቪኒሺየስ ጁኒየር የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ራፋ ሲልቫ ለቤኔፊካ ብቸኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።

የ15 ጊዜ የሻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ባለቤት ሪያል ማድሪድ በድምር ውጤት 3 ለ 1 በማሸነፍ ወደ ጥሎ ማለፍ ገብቷል።



በሌላኛው መርሐ ግብር ፒኤስጂ እና ሞናኮ ሁለት አቻ ተለያይተዋል።

ማርኪኒዮስ እና ክቪቻ ክቫራትስኬሊያ ግቦቹን ከመረብ ጋር አገናኝተዋል።

ማግነስ አክሊኡቼ እና ጆርዳን ቴዜ ለሞናኮ ጎሎቹን አስቆጥረዋል።

የሞናኮው ማማዱ ኩሊባሊ በ58ኛው ደቂቃ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።



የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ፒኤስጂ በአጠቃላይ ውጤት 5 ለ 4 በማሸነፍ ጥሎ ማለፉን ተቀላቅሏል።

ጁቬንቱስ ጋላታሳራይን 3 ለ 2 አሸንፏል።

በአሊያንዝ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ፌዴሪኮ ጋቲ እና ዌስተን ማኬኒ በጨዋታ ማኑኤል ሎካቴሊ በፍጹም ቅጣት ምት ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ቪክቶር ኦሲሜን በጭማሪ 3ዐ ደቂቃ እና  በ105ኛው እንዲሁም ባሪስ አልፐር ዪልማዝ በ119ኛው ደቂቃ ላይ የጋላታሳራይን ጎሎች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

የጋላታሳራዩ ሎይድ ኬሊ በ48ኛው ደቂቃ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።

ጋላታሳራይ በድምር ውጤት 7 ለ 5 በማሸነፍ የጥሎ ማለፍ ተሳትፎ ትኬቱን ቆርጧል።

ዛሬ አስቀድሞ በተካሄደ ጨዋታ አትላንታ ቦሩሲያ ዶርትሙንድን 4 ለ 1 አሸንፏል። አትላንታ በድምር ውጤት 4 ለ 3 በማሸነፍ ወደ ጥሎ ማለፍ ገብቷል።

የማጣሪያ የደርሶ መልስ ጨዋታዎቹን ተከትሎ ሪያል ማድሪድ፣ ፒኤስጂ፣ አትሌቲኮ ማድሪድ፣ ጁቬንቱስ፣ ኒውካስትል ዩናይትድ፣ አትላንታ፣ ቦዶ ግሊምት እና ባየር ሌቨርኩሰን ጥሎ ማለፉን ተቀላቅለዋል።

በውድድሩ አዲስ ፎርማት በሊግ ምዕራፍ ከአንድ እስከ ስምንት የወጡ ቡድኖች በቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፍ መግባታቸው ይታወቃል።

አርሰናል፣ ባየር ሙኒክ፣ ሊቨርፑል፣ ቶተንሃም ሆትስፐርስ፣ ባርሴሎና፣ ቼልሲ፣ ስፖርቲንግ ሊዝበን እና ማንችስተር ሲቲ በቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፍ የገቡ ቡድኖች ናቸው።

የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ እጣ ማውጣት ስነ ስርዓት አርብ የካቲት 20 ቀን 2018 ዓ.ም በስዊዘርላንድ ኒዮን ይካሄዳል።

በሚወጣው እጣ መሰረት የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች በመጋቢት ወር 2018 ዓ.ም ይካሄዳሉ።

ከጥሎ ማለፍ ጀምሮ የሚደረጉ ጨዋታዎች ከዚህ ቀደም በነበረው የውድድር ፎርማት መሰረት ይከናወናሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም