አትላንታ ወደ ጥሎ ማለፍ ገብቷል - ኢዜአ አማርኛ
አትላንታ ወደ ጥሎ ማለፍ ገብቷል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2018 (ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታ አትላንታ ቦሩሲያ ዶርትሙንድን 4 ለ 1 አሸንፏል።
በቤርጋሞ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ጂያንሉካ ስካማካ፣ ዴቪዴ ዛፓኮስታ እና ማሪዮ ፓሳሊች በጨዋታ ላዛር ሳማርድዚች በፍጹም ቅጣት ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ሳማርድዚች በ99ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠራት ጎል አትላንታን ወደ ቀጣይ ዙር አሳልፋለች።
ካሪም አዲዬሚ ለዶርትሙንድ ብቸኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
የዶርትሙንዱ ራሚ ቤንሴባይኒ በ98ኛው ደቂቃ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።
በጨዋታው አትላንታ በኳስ ቁጥጥር እና ግልጽ የግብ እድሎችን በመፍጠር የተሻለ ነበር።
ውጤቱን ተከትሎ የጣልያኑ ክለብ በድምር ውጤት 4 ለ 3 በማሸነፍ ጥሎ ማለፉን ተቀላቅሏል።
ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ዶርትሙንድ 2 ለ 0 ማሸነፍ ችሎ ነበር።
አትላንታ በመልሱ ጨዋታ ውጤቱን በመቀልበስ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል።