በአማራ ክልል በምርጥ ዘር ከለማው መሬት እስካሁን 131 ሺህ ኩንታል በላይ ዘር ተሰብስቧል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በምርጥ ዘር ከለማው መሬት እስካሁን 131 ሺህ ኩንታል በላይ ዘር ተሰብስቧል
ባህርዳር፤ የካቲት 18/2018(ኢዜአ)፦ በ2017/2018 የምርት ዘመን በምርጥ ዘር ከተባዛው መሬት ከ131 ሺህ ኩንታል በላይ ዘር መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በቅድመ-በልግ በዘር ከተሸፈነው የበቆሎ ማሳ የተሻለ ምርት እንጠብቃለን
የቢሮው የዘር ብዜት ባለሙያ አቶ ጥላዬ ሞገሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የዘር ብዜት ላይ በተለየ ትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
በምርት ዘመኑ በዘር ብዜት ከተሸፈነው ከ10 ሺህ 600 ሄክታር በላይ መሬት 232 ሺህ 589 ኩንታል ዘር ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
እስካሁን በተደረገው ጥረትም 131 ሺህ 676 ኩንታል የበቆሎ፣ የስንዴ፣ የሩዝ፣ የጤፍ፣ የማሽላ፣ የሰሊጥ፣ የቅባትና የጥራጥሬ እህል ዘር መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።
በአማራ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ፣ በዩኒየኖች፣ በግል ዘር አባዢዎችና ድርጅቶች የሚካሄደውን የዘር ብዜት እስከ መጋቢት ወር አጋማሽ ሰብስቦ በማጠናቀቅ ለአርሶ አደሩ ለማድረስ ዝግጅት እንደሚደረግ ነው የገለጹት።
እስካሁን በተደረገ የተቀናጀ ጥረትም የበቆሎ ዘር ፍላጎት ማሟላት መቻሉን ጠቁመው ሌሎች የሰብል ዘሮችን በሚፈለገው ልክ በማባዛት ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ዙሪያ ወረዳ በዘር ብዜት ተግባር የተሰማሩት አቶ ቢኒያም ሙላት፤ በ48 ሄክታር መሬት ላይ ያባዙትን የበቆሎ ዘር ሰብስበው ወደ መጋዘን እያጓጓዙ መሆኑን ተናግረዋል።
የምርት ዘመኑ ለዘር ብዜት ስራው አመቺ ሆኖ በመገኝቱ የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ አስችሎኛል ብለዋል።
በ62 ሄክታር መሬት ያባዙትን ቢኤች 561 የበቆሎ ዘር ጥራቱን በጠበቀ አግባብ ሰብስበው እያጠናቀቁ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የወንበርማ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሰማኸኝ ሽዋፈራው ናቸው።
ዘሩን በቀጣይ አበጥረውና በተለያየ መጠን አሽገው ለአርሶ አደሩ በወቅቱ ለማቅረብ እየተዘጋጁ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
በክልሉ በ2016/2017 የምርት ዘመን በዘር ከተሸፈነው 14 ሺህ ሄክታር መሬት 281 ሺህ ኩንታል ዘር በመሰብሰብ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።