በቅድመ-በልግ በዘር ከተሸፈነው የበቆሎ ማሳ የተሻለ ምርት እንጠብቃለን - ኢዜአ አማርኛ
በቅድመ-በልግ በዘር ከተሸፈነው የበቆሎ ማሳ የተሻለ ምርት እንጠብቃለን
ሀዋሳ፤ የካቲት 17/2018 (ኢዜአ) ፡-በዘር ከተሸፈነው የበቆሎ ማሳ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ቅድመ በልግ አብቃይ የሆኑ የሃዋሳ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡
የወረዳው እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት መምሪያ በበኩሉ በተፈጥሮ የሚገኘውን እርጥበት በማቆየት ቀድመው የበልግ እርሻ የሚጀመሩ ቀበሌዎች 96 ከመቶ የዘር ስራ አጠናቀው ወደ ኩትኳቶ ገብተዋል፡፡
በሲዳማ ክልል የሃዋሳ ዙሪያ ወረዳ በበልግ በስፋት በቆሎ ከሚያመርቱ ወረዳዎች ተጠቃሽ ሲሆን በወረዳው የሚገኙ ሰባት ቀበሌዎች በተፈጥሮ የሚገኘውን እርጥበት በመያዝ ቀድመው የበልግ እርሻ ይጀምራሉ፡፡
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የወረዳው አርሶ አደሮች፣በመስከረም ወር ላይ ከነበረው ዝናብ እርጥበት እንዲይዝ አድርገው ባዘጋጁት መሬት ላይ ከታህሳስ ወር ጀምሮ በቆሎ መዝራት ጀምረናል ብለዋል፡፡
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አርሶ አደር ስጦታ ሂርጳ በተገቢ ግብዓትና የባለሙያ ድጋፍ በዘር ከሸፈኑት 2 ነጥብ 5 ሄክታር ማሳ የተሻለ ምርት ለማግኘት አስፈላጊውን እንክብካቤ እያደረኩ ነው ብለዋል፡፡
በዘር ከሸፈኑት ማሳ በመጪው ግንቦት ወር ጀምሮ የበቆሎ እሸት ምርት ወደ ተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በመጫን እስከ ከ300 ሺህ ብር በላይ የሚደርስ ገቢ እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደር እስራኤል ባሳ በበኩላቸው በኩታ ገጠም በበቆሎ የሸፈኑት ማሳ ለኩትኳቶ መድረሱን ነው የሚገልጹት።
ከጊዜ ወደ ጊዜ የግብዓት አጠቃቀምንም ማሻሻል በመቻሉ የምርት እድገቱ መጨመሩን የጠቀሱት አርሶ አደሩ ከጓሮአቸው ከምርቱ 250 ሺ ብር ገቢ እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡
የወረዳው አርሶ አደሮች ከግብዓት አጠቃቀም ጋር ያላቸው ንቃተ ሂሊና ከፍተኛ በመሆኑ ምርታማነት እያደገ መምጣቱን የገለጹት ደግሞ የግብርና ልማት ባለሙያው አቶ ደስአለኝ ቲሮሬ ናቸው፡፡
ቅድመ በልግ አብቃይ በሆኑ ቀበሌዎች አስፈላገው ግብዓት በወቅቱ መድረሱንና የባለሙያ ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አዲሱ ደስአለኝ በበኩላቸው በወረዳው ከ12 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቅድመ በልግና በመደበኛ በልግ እርሻ በበቆሎ ዘር ለመሸፈን እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ውስጥም 3 ሺህ 912 ቅድመ በልግ አብቃይ በሆኑ ሻመና ክላስተር ሰባት ቀበሌዎች የሚለሙ ሲሆን በአካባቢዎቹ 96 ከመቶ የሚሆነው ማሳ በዘር ተሸፍኖ የእንክብካቤ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
በቅድመ በልግ አብቃይ የሆኑ ቀበሌዎች በተፈጥሮ እርጥበትን በማቆየት በቆሎ የሚዘሩና የበቆሎ እሸትንም ቀድመው ወደ ተለያዩ ቦታዎች በማድረስ ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የሚገልጹት።
በወረዳው ለቅድመ በልግና መደበኛ በልግ ከ3 ሺህ ኩንታል በላይ በቆሎ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ የቀረበ ሲሆን የግብርና ባለሙያዎችም ተገቢውን ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ኃላፊው ጨምረው ገልጸዋል፡፡