130ኛውን የዓድዋ ድል "ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ" በሚል መሪ ሀሳብ ለማክበር ዝግጅት ተጠናቋል - ኢዜአ አማርኛ
130ኛውን የዓድዋ ድል "ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ" በሚል መሪ ሀሳብ ለማክበር ዝግጅት ተጠናቋል
አዲስ አበባ፤የካቲት 17/2018 (ኢዜአ):- የዓድዋ ድል በዓል መከበር የኢትዮጵያዊነት የጥንካሬና የፅናት መሠረት ዳግም የሚታደስበት፤ለሀገራችን ሉዓላዊነትና አንድነት የገባነውን ቃል ኪዳን የምናጸናበት ነው ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሐመድ ገለጹ።
የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሐመድ 130ኛውን የዓድዋ ድል በዓል አከባበር አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም፥ የድል በዓሉን ''ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ'' በሚል መሪ ሐሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማክበር አስፈላጊውን ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል።
የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን የማይበገር ማንነት ማኅተም የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ፋናና የሰው ልጅ እኩልነት የተረጋገጠበት ዓለም አቀፋዊ ድል ነው ብለዋል።
130ኛውን የዓድዋ ድል በዓልን ስናከብር የኢትዮጵያዊነትን የጥንካሬና የፅናት መሠረት ዳግም የምናድስበት፣ ለሀገራችን ሉዓላዊነትና አንድነት የገባነውን ቃል ኪዳን የምናፀናበት ልዩ ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን በ1888 ዓ.ም በዓድዋ ተራሮች ላይ ዘር፣ቀለምና ሃይማኖት ሳይለያቸው ለአንዲት ሉዓላዊት ሀገር በኅብረት የቆሙበትና ተጋድሎ የፈጸሙበት የጋራ ድል መሆኑን ተናግረዋል።
የዘንድሮው መሪ ሐሳብ ትናንት በጀግኖች ደምና አጥንት የተጠበቀችውን ሀገር ዛሬ በዘላቂ ሰላምና በልማት ወደ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትና ከፍታ ለማሻገር ያለንን ፅኑ ቁርጠኝነት እንደሚገልጽ ተናግረዋል።
ጀግናው የመከላከያ ሠራዊትም የዓድዋን የጀግንነት ውርስ በመሰነቅ የሀገርን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥና ወደ ብሩህ አድማስ የምናደርገውን ጉዞ ለመጠበቅ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በዓሉን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ አህጉራዊና ሀገራዊ ሁነቶች መዘጋጀታቸውን ገልጸው የ'ዓድዋ ድምፆች' የወጣቶች መድረኮች፣ ስፖርታዊ ውድድሮች፣ ወታደራዊና ታሪካዊ ኤግዚቢሽኖች፣ ልዩ ልዩ የኪነ-ጥበብ ስራዎችና የዓድዋን ድል የሚዘክሩ ዘጋቢ ፊልሞች እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።
በዓሉ መላው ኢትዮጵያውያን የነገውን ብሩህ አድማስ በጋራ የሚያልሙበት ይሆናልም ብለዋል።