ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ክትትልና ቁጥጥር ስኬታማ ተግባር አከናውናለች

አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስ በሽታን ጨምሮ በሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ክትትልና ቁጥጥር ስኬታማ ተግባር እያከናወነች መሆኗን የአፍሪካ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል ገለፀ።


 

በማዕከሉ የወረርሽኝ መከላከል፣ ዝግጁነት እና ምላሽ ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ንጋሼ ንጎንጎ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስን ለመቆጣጠር  ያደረገችው ርብርብ ወረርሽኙን በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር አስችሏል።

ይህም ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጉዳት ሳይደርስ በሽታን መቆጣጠር እንደሚቻል ትምህርት የሚወሰድባት ያደርጋታል ብለዋል። 

አክለውም ሀገሪቱ በጤና ኤክስቴንሽን መርሐ-ግብር አማካኝነት የበሽታዎች ልየታ ማከናወን የሚያስችል ጠንካራ  የቅኝት ሥርዓት ዐቅም እንዳላት የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም ለሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቅኝትና ቁጥጥር ትምህርት የሚሆን ልምድና የዝግጁነት ዐቅም መፍጠሩን ጠቅሰዋል።

ማዕከሉ የኢትዮጵያ ጤና ዘርፍን ለማጠናከር በትብብር እየሠራ መሆኑንም ለኢዜአ አረጋግጠው፤ ለአብነትም የተለያየ የቴክኒክ እገዛ፣ የላቦራቶሪ ዐቅምን ማጠናከርና የግብዓት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

በአኅጉሪቱ የጤና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሀገር ውስጥ ሀብትን ማሳደግ፣ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማጎልበት፣ ውጤታማ አሠራርን ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም