ቀጥታ፡

በሚዛን አማን ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ለከተማዋ አዲስ ገጽታ እያጎናጸፈ ነው 

ሚዛን አማን፤ የካቲት 18/2018(ኢዜአ)፦ በሚዛን አማን ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት አዲስ እይታና ውብ ገጽታን ለከተማዋ እያጎናጸፈ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።

በከተማዋ ተጠናክሮ በቀጠለው የኮሪደር ልማት ስራ  የምዕራፍ ሁለት ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ  መሆኑን ከተማ አስተዳደሩ ገልጿል።

በሐዋሳ ከተማ በሁለተኛው ምዕራፍ የ8 ነጥብ 7 ኪሎ-ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነ ነው

ለኢዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል መምህር ዘማች ከበደ እንዳሉት፤ በከተማዋ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት አዲስ እይታና ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ያለ የልማት ተግባር ነው።


 

በአዲስ አበባና በሌሎች የክልል ከተሞች የተመለከቱት ስራ  በሚዛን አማንም መተግበሩ ያስደሰታቸው ሲሆን ይህም ከተማዋን ተወዳዳሪና ለኑሮ ተመራጭ እንደሚያደርጋትና የነዋሪውን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት እየተተገበረ ያለው የከተማ ኮሪደር ልማት እንደ ሀገር ፍትኃዊና ተቀራራቢ የሆነ የከተሞች ዕድገትን ለማምጣት የሚያስችል መሆኑን ማረጋገጣቸውን ጠቅሰዋል። 

በልማቱ እየታየ ያለው ለውጥ ተጠናክሮና ተስፋፍቶ እንዲቀጥል የሚናደርገውን ርብርብ እናጠናክራለን ብለዋል።

አቶ ተክሌ አንችአብ  በበኩላቸው፤ ከተማ ሊያድግና ሊለማ የሚችለው ኮሪደርና መሰል ፕሮጀክቶች በአግባቡ ሲተገበሩ እንደሆነ ተናግረዋል።


 

ከዚህ ቀደም ተደብቆ የነበረው የሚዛን አማን ከተማ ገጽታ በኮሪደር ልማቱ ውበት ጎልቶ እየወጣ መሆኑን መመልከታቸው ትልቅ ሐሴት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።

በከተማዋ የተገጠሙ ዘመናዊ የመንገድ ዳር መብራቶች ተጨማሪ ድምቀት ከመሆናቸውም ባሻገር ማታ ማታ ያለ ሰቀቀን ከቦታ ወደ ቦታ ለመንቀሳቀስ የሚያስችል መሆኑን አክለዋል።

ከዚህ ቀደም የመንገድ ጥበት ከእግረኛ መንገድ አለመኖር ጋር ተዳምሮ ከፍተኛ መጨናነቅ በከተማዋ ይስተዋል እንደነበር የገለጹት ደግሞ አቶ አደመ ገይናንስ የተባሉ ነዋሪ ናቸው።


 

አቶ አደመ የኮሪደር ልማቱ በተጠናቀቀባቸው መስመሮች ይህ ችግር ተቀርፎ ማየታቸውን ጠቅሰው ልማቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ድጋፍ እንደሚያደርጉ አክለዋል።

የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር ሰሎሞን ሌዊ፤ በከተማዋ የሚከናወነው የኮሪደር ልማት ስራ ገጽታዋን በመቀየር ለኑሮ ምቹ፣ ተስማሚና ተመራጭ ከማድረግ ባሻገር  ተወዳዳሪነቷንም እያሳደገ ነው ብለዋል።


 

አሁን ላይ በከተማዋ ከ5 ኪሎ ሜትር የሚበልጥ የሁለተኛ ምዕራፍ ኮሪደር ልማት ሥራ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

የመንገድ ዳር መብራት፣ የስማርት ፖል ተከላና የመስመር ዝርጋታ መከናወኑን ገልጸው የሦስተኛውን ምዕራፍ ለማስጀመር የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል።

ከኮሪደር ልማቱ ጋር የሳር ተከላ፣ የማረፊያ ወንበርና ጥላ እንዲሁም የአረንጓዴ መናፈሻ እየተሠራ ሲሆን ከተማዋን ለነዋሪዎች ውብና ማራኪ እንዲሁም ምቹ አድርጎ የመገንባት ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ገልጸዋል።

የሚዛን አማን ከተማ በቅርቡ ከተመረቀው የደንቢ ኢኮ ሎጅ እና በመጠናቀቅ ላይ ካለው የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ ጋር ተዳምሮ ተጨማሪ የዕድገትና መስፋት ዕድልን የያዘች ከተማ መሆኗ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም