በሐዋሳ ከተማ በሁለተኛው ምዕራፍ የ8 ነጥብ 7 ኪሎ-ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሐዋሳ ከተማ በሁለተኛው ምዕራፍ የ8 ነጥብ 7 ኪሎ-ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 16/2018(ኢዜአ)፦በሐዋሳ ከተማ በሁለተኛው ምዕራፍ የ8 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ በተሳለጠ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሚገኝ የከተማዋ ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከተማዋን በጎበኙበት ወቅት ያስተላለፉት መልዕክት በከተማዋ እየተከናወነ ላለው የኮሪደር ልማት ትልቅ አቅምና መነሳሳትን የሚፈጥር መሆኑን ከንቲባው ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በሐዋሳ ከተማ በሁለተኛው ምዕራፍ የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን መጎብኘታቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት የኮሪደር ልማት ሥራዎች የተሻለች ሀገርን ለትውልድ የመገንባት አካል መሆናቸውንና በርካታ ከተሞችን እየለወጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት በ8 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር መንገድ ላይ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት መሠረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶችን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ የሚያደርጉ መሠረተ ልማቶችን ያቀፈ ነው።
ይህ የልማት ሥራ የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ የነዋሪዎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ያለመ መሆኑን አብራርተዋል።
የከተማዋን የትራንስፖርት ፍሰት ለማሳለጥና የተሽከርካሪ መጨናነቅን ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም የትራፊክ ፍሰትን የሚያቀላጥፉ 5 አዳዲስ የተሽከርካሪ ተርሚናሎች መገንባታቸውን ጠቁመው ከዚህ ቀደም በከተማዋ ያልነበሩ 13 ዘመናዊ የተሽከርካሪ ማቆሚያ (ፓርኪንግ) ቦታዎችም መገንባታቸውን ጠቁመዋል፡፡
ሐዋሳ የቱሪስትና የኮንፍረንስ ከተማ መሆኗን ያነሱት ከንቲባው፤ ለጎብኚዎችም ሆነ ለነዋሪዎች ምቹ የሆነ የእግር መንገድ መዘርጋቱን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ 17 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የእግረኛ መንገድ መገንባቱን ጠቅሰው ከዚህ ውስጥ 2 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የሚሆነው መንገድ እስከ 7 ሜትር የሚደርስ ስፋት ያለውና ለእግር ጉዞ እጅግ ምቹ ሆኖ የተሠራ ነው።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተከናወነው የኮሪደር ልማት ለሐዋሳ ከተማ ትልቅ ልምድና ተሞክሮ መሆኑን አቶ ጥራቱ ገልጸዋል።
ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በጥራትና በአጭር ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ እንደሚቻል የታየበትን ይህንኑ ተሞክሮ በመጠቀም በሐዋሳም ሥራዎች በተሳለጠ ሁኔታ ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡