ቀጥታ፡

በዞኑ በጤና ጣቢያዎች ደረጃ መሰጠት የጀመረው በቀዶ ሕክምና የማዋለድ አገልግሎት የእናቶችና ህጻናትን ጤና ለማሻሻል አግዟል

ወልዲያ ፤ የካቲት 17/2018(ኢዜአ)፦በሰሜን ወሎ ዞን በጤና ጣቢያዎች ደረጃ መሰጠት የጀመረው በቀዶ ሕክምና የማዋለድ አገልግሎት የእናቶችን እና ህጻናትን ጤና ለማሻሻል እያገዘ መሆኑን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ። 

የጤና መምሪያው ኃላፊ ሲስተር ፈለቁ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት፣በዞኑ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋፋት የእናቶችና ህፃናት ጤና ላይ መሻሻል መጥቷል።

በሆስፒታሎች ብቻ ተወስኖ የነበረውን በቀዶ ሕክምና የማዋለድ አገልግሎት፣ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን በመመደብና የሕክምና ቁሳቁሶችን በማሟላት በጤና ጣቢያዎችም መሰጠት መጀመሩን አመልክተዋል።

በዚህም ባለፉት ሰባት ወራት በዞኑ የቀዶ ጥገናን ጨምሮ በጤና ተቋማት ከ22 ሺ በላይ እናቶች በሰለጠነ ባለሙያ የታገዘ የህክምና አገልግሎት ተሰጥቷል ብለዋል። 

ኢትዮጵያ በሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ክትትልና ቁጥጥር ስኬታማ ተግባር አከናውናለች

ከእነዚህ ወስጥ ከአንድ ሺ በላይ የሚሆኑት በስድስት ጤና ጣቢያዎች በቀዶ ህክምና የወሊድ አገልግሎት ያገኙ እናቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።

በጤና ጣቢያዎች የቀዶ ህክምና አገልግሎት መሰጠቱ እናቶች በሪፈራል ምክንያት ይደርስባቸው የነበረውን እንግልት መቀነሱን ገልጸዋል።

የሳንቃ ከተማ ነዋሪዋ ያለምዘውድ መንገሻ በበኩላቸው፣ ቀደም ሲል ለወሊድ ወደ ወልዲያ ይጓዙ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን በአቅራቢያቸው በሚገኘው ሳንቃ ጤና ጣቢያ አገለግሎት እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል። 

በጤና ጣቢያው መንታ ልጆችን ያለምንም እንግልት በሰላም መገላገላቸውንም ተናግረዋል።

በሃራ ጤና ጣቢያ በቀዶ ሕክምና የወሊድ አገልግሎት ያገኙት ዘምዘም ሃሰን፤  አገልግሎቱ በአካባቢያቸው መሰጠቱ እፎይታ እንደሰጣቸው ገልጸዋል።

እናቶች የመውለጃ ጊዜያቸው ሲደርስ ያለምንም ጭንቀት በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ጤና ጣቢያ መሄድ የሚችሉበት ዕድል በመፈጠሩ መደሰታቸውንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም