በሃሳብ የበላይነት ላይ የተመሰረተ ፉክክር ለማድረግ ተዘጋጅተናል - ተፎካካሪ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
በሃሳብ የበላይነት ላይ የተመሰረተ ፉክክር ለማድረግ ተዘጋጅተናል - ተፎካካሪ ፓርቲዎች
ባህር ዳር፤ የካቲት 17/2018(ኢዜአ)፦በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሃሳብ የበላይነት ላይ የተመሰረተ ፉክክር ለማድረግ መዘጋጀታቸውን በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ።
ፓርቲዎቹ ጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የሰሜን ኢትዮጵያ አስተባባሪ ኃይለማርያም ብርሃኑ፤ ምርጫው የሕዝብ ድምፅ የሚከበርበት ሁሉን አቀፍና አካታች እንዲሆን ፓርቲያቸው ሃላፊነቱን እንደሚወጣ ገልጸዋል።
ፓርቲያቸው ለአባላቱና ለደጋፊዎቹ በምርጫ ሥነ-ምግባር ላይ ግንዛቤ እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው፣ በምርጫው ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በሕግ አግባብና በሀሳብ የበላይነት ብቻ ለመፍታት በአጽንኦት እየሰራን ነው ብለዋል።
ስልጣን በህዝብ ድምጽ በምርጫ ብቻ የሚመጣ በመሆኑ በአቋራጭ ሥልጣን ለመያዝ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ፓርቲያቸው በጽኑ እንደሚያወግዝም አመልክተዋል።
በብሔራዊ ጥቅም ላይ አንደራደርም- ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች
ፓርቲዎች በጋራ ባፀደቁት የምርጫ ሕግና ደንብ በመገዛት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ተአማኒ እንዲሆን የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) የአማራ ክልል የሥራ አስፈፃሚ አመራር አብደላ ስመኘው(ዶ/ር) ናቸው።
ፓርቲያቸው የምርጫ ሥነ-ምግባር ደንቡን ለአባላቱና ለደጋፊዎቹ እየስተዋወቀ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ በሐሳብ የበላይነት ለማሸነፍና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካን ለማራመድ በትጋት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ለተሻለ ሀገረ መንግስት ግንባታ ሁሉም የተሻለ ሀሳብ ማዋጣት እንዳለበት ገልጸው፣ጠቅላላ ምርጫው ሀገርን ያስቀደመና የሀሳብ የበላይነት የሚያሸንፍበት እንዲሆን እንሰራለን ብለዋል።
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የምዕራብ ጎጃም ዞን የፋይናንስ ክፍል ሃላፊ ይርጋ ሞገስ በበኩላቸው፣ ሀገርና ህዝብን ማሻገር የሚያስችል ስልጣን የሚገኘው በምርጫ ብቻ በመሆኑ ፓርቲያቸው በሀሳብ የበላይነት ለመፎካከር መዘጋጀቱን አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።