ቀጥታ፡

በብሔራዊ ጥቅም ላይ አንደራደርም- ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች

አዲስ አበባ፤ የካቲት 17/2018(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ እንደራደርም ሲሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።       

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ አጀንዳ ነው። በተለይ ብሔራዊ ጥቅምን ማስከበር ሊሂቃንና የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ሲሆን ሀላፊነቱ እጥፍ ድርብ ነው። 

በዚህም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምንም እንኳን የርዮተዓለም ልዩነትና የተለየ የፖሊሲ አተያይ ቢኖራቸው የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ግን ሁሉም እንደማይደራደሩ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ህያው ማሳያ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

የተለያዩ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የነቃ ተሳትፎ ሊያደርግ ይገባል።       

የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወይዘሮ ነቢሃ መሀመድ እንደሚሉት፤ፓርቲው የጋራ በሆኑና ኢትዮጵያን አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ በንቃት እየተሳተፈ ነው።     

የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር መጨመር እና እያደገ የመጣው ኢኮኖሚ ተከትሎ የባህር በር አስፈላጊ መሆኑን ፓርቲው ያምናል ያሉት ኃላፊዋ መንግሥት ያቀረበው የባህር በር ጥያቄን እንደግፋለን ብለዋል።    

ኢትዮጵያ መርህን ተከትላ በዲፕሎማሲው የባህር በር ባለቤትነትን ለማረጋገጥ ያቀረበችው ጥያቄ ውጤት እንዲያመጣ ነጻናትና እኩልነት ፓርቲ ከመንግሥት ጋር ተባብሮ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።  

ኢትዮጵያን ሊወር የመጣን ኃይል ኢትዮጵያዊያን ብሄር፣ ኃይማኖት እና ፆታ ሳይገድባቸው አንድ ሆነው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አስከብረዋል ያሉት ወይዘሮ ነቢሃ፤ በባህር በር ጉዳይም ይሄ አንድነት ሊደገም ይገባል ብለዋል።     

የአማራ ዲሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ ሊቀ መንበር ተስፋሁን ዓለምነህ በበኩላቸው፤ የትኛውም የፖለቲካ ልዩነት ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም በላይ ሊሆን አይችልም ሲሉ ተናግረዋል።  

ያለን የፖለቲካ አተያይ አልያም ርዮተዓለም የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥል መሆን የለበትም፤ ፓርቲያችን በዚህ ላይ የጸና አቋም አለው ብለዋል። 

የብሄራዊ ጥቅም የሕልውና ጉዳይ ነው፤ ህልውና ደግሞ ለድርድር አይቀርብም ያሉት ሊቀ መንበሩ፤ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም መከበር የሚከፈለውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል ፓርቲያችን ዝግጁ ነው ብለዋል።      

የወለኔ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ-መንበር ፈይሰል አብዲላዚዝ፤ የባህር በር ጥያቄ ተገቢና የሕዝብ ጥያቄ መሆኑን ፓርቲው እንደሚገነዘብ ይገልጻሉ።  

ፓርቲው ጥያቄው ተቀባይነት አግኝቶ የኢትዮጵያ መሻት እንዲሳካ ከመንግሥት ጎን እንደሚቆምም ነው ያረጋገጡት።  

በብሄራዊ ጥቅም አጀንዳ ዙሪያ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አንድ ሆኖ በንቃት ሊሳተፍበት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።    

የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን ታፈሰ በበኩላቸው፤ በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ሀገር ለምታቀርብልን ጥሪ ሁሌም ዝግጁ ነን ብለዋል።  

ፓርቲው ለልማት፣ ለሠላም እና ሀገራዊ ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሰራ ጠቁመው፤ በዚህ ዙሪያም ከመንግሥት ጋር ተባብሮ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል። 

   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም