የሐዋሳ የኮሪደር ልማት ከተማዋን ምቹ የሥራ፣ የመኖሪያና የመዝናኛ ማዕከል እያደረጋት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሐዋሳ የኮሪደር ልማት ከተማዋን ምቹ የሥራ፣ የመኖሪያና የመዝናኛ ማዕከል እያደረጋት ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 17/2018(ኢዜአ)፦የሐዋሳ የኮሪደር ልማት ከተማዋን የተሟላ ውበት በማላበስ ምቹ የመኖሪያና የመዝናኛ ማዕከል እያደረጋት ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገለጹ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት በአሁኑ ወቅት ወደ ክልሎች ተስፋፍቶ በርካታ ከተሞችን ተደራሽ አድርጓል፡፡
በሐዋሳ ከተማም በሁለተኛው ምዕራፍ ሰፊ የኮሪደር ልማት አየተከናወነ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ልማቱን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
በሐዋሳ ከተማ በሁለተኛው ምዕራፍ የ8 ነጥብ 7 ኪሎ-ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነ ነው
በሐዋሳ ከተማ የተከናወነውንና በመከናወን ላይ ያለውን የኮሪደር ልማት በተመለከተም ኢዜአ የነዋሪዎችን አስተያየት ጠይቋል።
የሐዋሳ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ሃይማኖት ጌታቸው፤ በርካታ የከተማዋ አካባቢዎች ከዚህ ቀደም ጨለማ፣ የቆሻሻ መጣያ፣ በምሽት ለመንቀሳቀስ የማይመቹ እንደነበሩ ታስታውሳለች።
በቃሉ መሠረት በበኩሉ፤ የተሽከርካሪና የእግረኛ መንገዶች ደረጃቸውን ያልጠበቁ በመሆናቸው ለትራፊክ መጨናነቅ ችግር ሆነው መቆየታቸውን ገልጿል።
እንዲሁም በውስጥ ለውስጥ መንገዶች መብራት ባለመኖሩ ሰዎች በምሽት ለመንቀሳቀስ ስጋት እንደነበረባቸው አውስቷል።
አሁን ያ ሁሉ በሀዋሳ ከተማ ታሪክ ሁኗል የምትለው ሃይማኖት ጌታቸው፤ ሐዋሳ ደምቃ ተውባለች ስትል ሀሳቧን አጋርታለች።
ሰፋፊ የእግረኛ፣ የተሽከርካሪና የብስክሌት መንገዶች እንዲሁም የስፖርት ማዘውተሪያዎች መገንባታቸውን የገለጸው ልዑል በላይነህ፥ ለከተማዋ ነዋሪዎች ከመዝናኛ እስከ ሥራ ቦታ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ጠቅሷል። የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ገፅታ በእጀጉ መቀየሩንም ነው የተናገረው።
በቃሉ መሰረት በበኩሉ፤ ልማቱ ህጻናትንና አዛውንቶችን ጨምሮ በአጠቃላይ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑን ተናግሯል።
በወቅቱ በአካባቢው የሰርግ ፎቶ ፕሮግራም እያከናወኑ ያገኘናቸው ተክሌ ሸዋ እና ሰብለ መንገሻ የኮሪደር ልማቱ ለከተማዋ የሰጣት ገጽታ ለፎቶ ፕሮግራማቸው ልዩ ድምቀት እንደሆነላቸው ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ለፎቶግራፍ ተስማሚ የሆኑ ቦታዎች ውስን እንደነበሩ አስታውሰው፤ አሁን ግን በልማቱ ምክንያት ከተማዋ ሙሉ በሙሉ ውብ ገፅታ በመላበሷ ለፎቶ ቀረጻ እጅግ ማራኪ ሆናለች ብለዋል።
የከተማዋ ጽዳትና ውበት ለሙሽሮች ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም ጎብኝ ልዩ የሆነ ደስታና የአእምሮ እረፍት እንደሚሰጥም ነው ሙሽሮቹ የገለፁት።
ልማቱ ወጣቶች አልባሌ ቦታዎች ከማሳለፍ ይልቅ ንጹህ አየር ወደሚያገኙባቸውና ደረጃቸውን ወደጠበቁ መናፈሻዎች እንዲያመሩ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
ለሁሉም ክፍት እና ውብ የሆኑ የጋራ ቦታዎች መኖራቸው ሰዎች ጤናማ በሆነ መንገድ እንዲገናኙና ማህበራዊ ትስስራቸውን እንዲያጠናክሩ እንደሚያግዝም ነው የገለጹት።
የተሰራው ልማት ውብና በአረንጓዴ የተሞላ መሆኑ ለጸሐፊዎች፣ ለተማሪዎችና ለፈጠራ ባለሙያዎች ምቹ ድባብ መፍጠሩን በመግለጽ የስራ ባህልን ሙሉ ለሙሉ መቀየሩን እና የተሰራበት ፍጥነትም የአመራሩን የመሪነት ብቃትና የወጣቶችን ትጋት ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።