ቀጥታ፡

ፕሮግራሙ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች ጥሪት በማፍራት ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡ አስችሏል

ኮምቦልቻ፤ ታህሳስ 21/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች ጥሪት በማፍራት  ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡ ማስቻሉን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ገጠር ክላስተር አስተባባሪ  ድረስ ሳህሉ(ዶ/ር)  ገለጹ። 

የክልሉ ግብርና ቢሮ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም የ5ኛው ምዕራፍ የማጠቃለያ መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ ዛሬ ተካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት ድረስ ሳህሉ(ዶ/ር) እንዳመለከቱት፤ በክልሉ ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት ለመውጣት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖች  በዘላቂነት በማቋቋምና ኑሯቸውን በማሻሻል ተጠቃሚ ማድረግ ያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም  በአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ፣ በሌማት ትርፋትና ሌሎችም ገቢ ማስገኛ ዘርፎች በመሰማራት በሚያገኙት ገቢ ራሳቸውን ከመቻል ባለፈ ጥሪት በማፍራት ላይ  እንደሆኑ አንስተዋል።

ፕሮግራሙ  ጠንካራ የሥራ ባሕል እንዲያጎለብቱ በማድረግ  ጠባቂነትን እያስቀረ የሚገኝ መሆኑንም ተናግረዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ  ደረጀ ማንደፍሮ በበኩላቸው፤ ፕሮግራሙ ምርታማነትን በማሳደግ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።


 

በፕሮግራሙ የታቀፉ ወገኖች በአዋጭ የሥራ መስክ ላይ ተሰማርተው የዘላቂ ማቋቋሚያ የገንዘብ መደገፍ በማግኘት  ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ መደረጉን አስረድተዋል።

ዘንድሮም ከ196 ሺህ  በላይ አባወራዎችና እማወራዎች ከፕሮግራሙ ተመርቀው በእንስሳት እርባታና  ማድለብ፣ በንብ ማነብ፣ በመስኖ ልማት፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማትና ሌሎች አገልግሎት ዘርፎች ይሰማራሉ ብለዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት መውጣት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ  አሊ መኮንን ናቸው።

ለዚህም የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም  በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ ወገኖችን በመደገፍና በተለያዩ ሥራዎች በማሰማራት በምግብ ራሳቸውን ከመቻል ባለፈ ምርት ለገበያ ለማቅረብ የሚያስችል አቅም መፍጠሩን አስረድተዋል።

በመድረኩ ላይ የክልል፣ የሰሜን እና  ደቡብ ወሎ ዞኖች፣ የዋግኽምራና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደሮች አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም