የመንግስት የፖሊሲ ማሻሻያዎች ለአምራች ኢንዱስትሪው ዕድገት ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስት የፖሊሲ ማሻሻያዎች ለአምራች ኢንዱስትሪው ዕድገት ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2018 (ኢዜአ)፡- የመንግስት የፖሊሲ ማሻሻያዎች ለአምራች ኢንዱስትሪው ዕድገት ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ቢሮ ያዘጋጀው ከተማ አቀፍ የኢትዮጵያ ታምርት ኤግዚቢሽንና ባዛር የመክፈቻ መርኃ ግብር እየተካሄደ ነው።
አዲስ አበባን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ውጤታማ ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶችን እያስገኙ ነው
በመርኃ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል እና ሌሎች የዘርፉ ተዋንያን ተገኝተዋል።
ለአንድ ሳምንት የሚቆየው ኤግዚቢሽንና ባዛር "ኢትዮጵያ ታምርት፤ አዲስ አበባ ትበልፅግ" በሚል መሪ ቃል በአዲስ አለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ተከፍቷል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ መንግሥት የአምራች ዘርፉን የሀገር ሉዓላዊነትና የጠንካራ መንግሥት መገለጫ አድርጎ ይመለከተዋል፡፡
አባቶቻችን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ነጻነት ለማስከበር ዓድዋ ላይ ያስመዘገቡትን ጀብዱ መንግስት በኢኮኖሚው መስክ ለመድገም ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
መንግሥት ለዚህ ስኬት ቁልፍ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ከማድረግ ጀምሮ የዘርፉን እድገት የሚያሳልጡ የተለያዩ ኢንሼቲቮችን ገቢራዊ አድርጓል ብለዋል፡፡
የአምራች ዘርፉ የጠንካራ ኢኮኖሚ መሠረት መሆኑን በማንሳት፤ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ወሳኝ ርምጃዎች የአምራች ኢንዱስትሪው ሀገር አቀፍ የማምረት አቅም አጠቃቀም 66 ነጥብ 3 በመቶ መድረሱን አስታውቀዋል።
በዚህም በኢትዮጵያ የሚመረቱ በርካታ ምርቶች ለታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በግብዓትነት እያገለገሉ መሆኑን ገልጸው፤ አፈጻጸሙን ከዚህ በላይ ለማሳደግ መትጋት ይገባል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዕድገት ከኢንዱስትሪ ዕድገት ጋር በእጅጉ የተሳሰረ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ከተማዋ የማምረቻ ማዕከል እንድትሆን በቅንጅት እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
የምርቶችን ጥራት፣ መጠንና ብዝሃነት በማሳደግ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ማድረግ፣ የፈጠራ ሥራዎችን በማበረታታት የማምረቻ መሣሪያዎችን በሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ማጎልበት የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ የአምራች ዘርፉ ተዋንያን አጋርነታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቀርበዋል፡፡