ቀጥታ፡

አዲስ አበባን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ውጤታማ ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶችን እያስገኙ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2018 (ኢዜአ)፡- አዲስ አበባን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ውጤታማ ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶችን እያስገኙ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡ 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ቢሮ ያዘጋጀው ከተማ አቀፍ የ“ኢትዮጵያ ታምርት” ኤግዚቢሽንና ባዛር በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል የመክፈቻ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው፡፡

የመንግስት የፖሊሲ ማሻሻያዎች ለአምራች ኢንዱስትሪው ዕድገት ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ ነው

“ኢትዮጵያ ታምርት፤ አዲስ አበባ ትበልፅግ” በሚል መሪ ሀሳብ በተሰናዳው በዚህ መርኃግብር ላይ የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለሀገር ሉዓላዊነት መከበርና ለብልፅግና መረጋገጥ መሰረታዊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አዲስ አበባን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ከንቲባዋ፤ በተለይም ከለውጡ ወዲህ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶች አበረታች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ሁሉን አቀፍ የለውጥ ጉዞ የሚሰምረው ምርትና ምርታማነት ሲያድግ ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ ይህንንም አሁን ላይ በተጨባጭ በውጤት እያየነው እንገኛለን ብለዋል፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የመዲናዋ ቀዳሚ የትኩረት መስክ መሆኑን ገልጸው፤ ለዘርፉ እድገት እንቅፋት የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት አስተዳደሩ በቁርጠኝነት ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል። 


 

ከተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት መካከል ለኢንዱስትሪዎች የሚሆን የመስሪያ ቦታን ማመቻቸት፣ አምራቾች የገንዘብ አቅርቦት እንዲያገኙ ድጋፍ ማድረግ እንዲሁም የፈጠራ ባለቤቶችን በመደገፍ የዘርፉን ተግዳሮቶች መቅረፍ ለአብነት አንስተዋል፡፡ 

አስተዳደሩ ፈጣንና አካታች ኢኮኖሚ ለመገንባት የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ሚና የማሳደግ እቅድ ይዞ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በመጪዎቹ ዓመታት ዘርፉ የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት እንዲሆን የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው፤ በከተማዋ የሚከናወኑ የልማት ተግባራት በሙሉ ሁለንተናዊ ለውጥን ዓላማ ያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የሚገኙ አምራቾች የሀገር ውስጥ ግብዓት አጠቃቀማቸው 45 በመቶ መድረሱን ጠቁመው፤ ይህም የዜጎችን የሀገር ውስጥ ምርት የመጠቀም ባህል በከፍተኛ ደረጃ እየለወጠው መሆኑን ገልጸዋል።


 

በመዲናዋ 3 ሺህ 890 የሚደርሱ ኢንዱስትሪዎች እንደሚገኙና እነዚህም ለከተማዋ የኢኮኖሚ እድገት የላቀ ድርሻ እያበረከቱ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህ ንቅናቄ ምርትን ከማስተዋወቅ ባለፈ በአምራች ዘርፉ የሚታዩ ተግዳሮቶችን በመለየት ረገድ ችግር ፈቺ መፍትሔዎችን እያመጣ እንደሚገኝና ለዘርፉ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።

አዲስ አበባ ሁሉም ኢንዱስትሪዎች በስፋት የሚያብቡባት ማዕከል እንድትሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

መንግስት የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ለማሳደግና የከተማዋን የኢኮኖሚ መዋቅር ስር ነቀል በሆነ መልኩ ለመቀየር የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ይህ ለአንድ ሳምንት የሚቆየው ኤግዚቢሽንና ባዛር የሀገር ውስጥ ምርቶችን ለህዝብ ከማስተዋወቅ ባለፈ፣ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ሰፊ የገበያ ትስስር እንደሚፈጥር ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም