የኮሪደር ልማቱ ለሥራ እና ለኑሮ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የኮሪደር ልማቱ ለሥራ እና ለኑሮ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል
ቡታጅራ፤ የካቲት 14/2018 (ኢዜአ)፦ የኮሪደር ልማቱ ከተሞችን ከማስዋብ ባለፈ ለሥራ እና ለኑሮ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የሆሳዕና፣ የቡታጅራና የወልቂጤ ከተሞች ከንቲባዎች ተናገሩ።
በሐዋሳ ከተማ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት ለነዋሪዎች በርካታ ዕድሎችን ይዞ መጥቷል
የሆሳዕና ከተማ ከንቲባ ሳሙኤል ሽጉጤ እንዳሉት፤ የኮሪደር ልማቱ የሆሳዕና ከተማን ለዕይታ ማራኪ፣ ለኑሮ ምቹ እና የኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭነቷን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል።
የቡታጀራ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አብዱ አሕመድ በበኩላቸው፤ ለኮሪደር ልማት ሥራው የሕብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ በመሆኑ ለስኬት መብቃቱን ገልጸዋል።
የወንዝ ዳርቻዎችን በማስዋብ የመዝናኛ ስፍራ በማድረግ ተሸፍኖ የቆየውን የከተማዋን ውበት መግለጥ መቻሉንም ጠቅሰዋል።
የኮሪደር ልማቱ ወደ ኋላ ቀርቶ የነበረውን የወልቂጤ ከተማ እድገት ለማስጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ያረጋገጡት ደግሞ የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ ሙራድ ከድር ናቸው።
ከተማዋ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድባትና ወደ ሌሎች አካባቢዎች የሚያልፉ ተጓዥች ማረፊያ በመሆኗ እንግዶች ተጨማሪ ጊዜን እንዲያሳልፉ የኮሪደር ልማቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።
በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ስንታየሁ ወልደሚካኤል በበኩላቸው፤ በክልሉ በሰባት ከተሞች በኮሪደር ለማልማት ከታቀደው 165 ኪሎ ሜትር ውስጥ እስካሁን 47 ኪሎ ሜትር መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
የኮሪደር ልማቱ የከተሞቹን ንፅህናና ውበት ከማስጠበቅ ባለፈ፤ የአረንጓዴ ቦታዎች፣ የሕዝብ መዝናኛዎችና ማረፊያዎችን በመፍጠሩ ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ማድረጉንም ለኢዜአ አረጋግጠዋል።