ቀጥታ፡

በሐዋሳ ከተማ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት ለነዋሪዎች በርካታ ዕድሎችን ይዞ መጥቷል

ሐዋሳ፤ የካቲት 14/2018 (ኢዜአ)፦ በሐዋሳ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት ከውበት፣ ከስራ ዕድል ጋር በተያያዘ ለከተማዋ በርካታ ዕድሎችን ይዞ መምጣቱን ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ።

ሶስተኛው ዙር የኮሪደር ልማት በጥራትና በፍጥነት የተሻሉ ስራዎች የሚከናወኑበት መሆኑንም የከተማዋ ከንቲባ አስታውቀዋል።

የበርካታ ቱሪስት መስህብ ስፍራዎች ባለቤት የሆነችው ሀዋሳ ከተማ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በስፋት እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ የበለጠ አዲስ ውበትን አላብሷታል።

በኮሪደር ልማቱ ማምሻቸውን በመዝናናት ላይ ከነበሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ኢዜአ ቆይታ ባደረገበት ወቅት ነዋሪዎቹ እንደገለፁት የኮሪደር ልማቱ ለከተማዋ በርካታ ዕድሎችን ይዞ መጥቷል።

የሰርጋቸውን ፎቶ ለመነሳት ከአርቤጎና የመጡት አቶ ክፍሌ ዋቀዩ እና ወይዘሪት አንድነት አየለ፤ የኮሪደር ልማቱ ከተማዋ በእጅጉ ውበትን እንድትጎናፀፍ አድርጓታል።


 

ለሰርጋችን ለምንነሳው የማስታወሻ ፎቶ ያማረ ገጽታ እንዲኖረው አድርጓል ነው ያሉት ሙሽሮቹ።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አቶ ጥበቡ ደሳለኝ፤ የኮሪደር ልማቱ ጎልቶ ያልወጣውን የከተማዋን ፀጋ ባማረ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረጉ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመዝናናት እንደመጡ ይናገራሉ።

በተለይም በምሽትም ሆነ በቀን ለመዝናኛነት ተመራጭ እንድትሆን ያደጉ የልማት ስራዎችን ለማየት መቻላቸውን ነው የገለጹት።

የሀዋሳ ከተማዋ ነዋሪ የሆነው ወጣት አማኑኤል አለሙ፤ የኮሪደር ልማቱ ከውበት ባለፈ ለበርካታ ስራ አጥ ወጣቶች የስራ ዕድል እየፈጠረ መሆኑን በተጨባጭ እየተመለከተ መሆኑን ነው የሚገልፀው።

በኮሪደር ልማቱ የተገነቡት የመዝናኛ ስፍራዎች የስራ ባህልን ከመቀየር ባሻገር ለከተማዋ ተጨማሪ ገቢ ያስገኘ መሆኑንም ነው የሚናገረው።

ሌላው አስተያየት ሰጪ ጃክ ፒተር በበኩሉ የኮሪደር ልማቱ በተለይ ለእግረኛም ሆነ ለተሽከርካሪና ምቹ ያልነበሩት መንገዶች ውበትን ተላብሰው አገልግሎት እንዲሰጡ አድርጓል ነው ያለው።

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው፤ ሶስተኛውን ዙር የኮሪደር ልማት ስራ የሌሎች ከተሞችን ተሞክሮ በመቀመርና ነዋሪውን በማስተባበር በጥራትና በፍጥነት ለማካሔድ እየተሰራ ነው።

በተለይ አመራሩ ከነዋሪው፣ ከባለሀብቱና ከመንግስት ሰራተኛው ጋር በመሆን ከተማዋን በጋራ ለመለወጥ እየሰሩ መሆኑንም ገልፀዋል።


 

በአሁኑ ወቅትም በሶስተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ፕሮግራም ከሀዋሳ ሀይቅ እስከ ሳውዝ ስታር አደባባይ የ3 ኪሎ ሜትር የኮሪደር መንገድ እየተገነባ ነው ብለዋል።

በሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ሲከናወን የነበረው ከ5 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሆነው የመንገድ ተግንባታ በተያዘው ሳምንት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆንም አረጋግጠዋል።

የኢዜአ የዲጂታል ሚዲያ ገጾች 👉 https://linktr.ee/ENADigital

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም