የኢትዮጵያ ዐሻራ ከዓድዋ - እስከ አፍሪካ ኅብረት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዐሻራ ከዓድዋ - እስከ አፍሪካ ኅብረት
በሙሴ መለሰ
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የፖለቲካ፣ የታሪክ እና ዲፕሎማሲ ምኅዳር ውስጥ ልዩ ስፍራ እና ተጽዕኖ ያላት ሀገር ናት።
የጥንታዊ ሥልጣኔዎች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ፤ በቅኝ ያልተገዛች ብቸኛ የአፍሪካ ሀገር ከመሆኗ ባሻገር ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መስፋፋት ትልቅ ሚና ተጫውታለች። ይህንም ታሪክ ይዘክራል።
39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ዛሬ ይጀመራል
አይበገሬነት፣ ሉዓላዊነት እና የፓን አፍሪካ መንፈስ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ካሳረፈቻቸው ዐሻራዎች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። በዘመናዊው ዓለምም በአፍሪካ አጀንዳዎች ላይ ወሳኝ ሚና እየተጫወተች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነት እና ማንነት ተምሳሌት
ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1896 በዓድዋ ጦርነት በጣሊያን ኃይሎች ላይ የተቀዳጀችው ድል በአፍሪካ እና በጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ነው።
አብዛኛው የአፍሪካ አኅጉር በቅኝ ግዛት ውስጥ በነበረበት ወቅት ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ድል ሉዓላዊነቷን ከማስጠበቅ ባለፈ በአፍሪካ እና በአፍሪካ ዳያስፖራ የነጻነት ትግሎች እንዲቀጣጠሉ አድርጓል።
በተለይም ከ20ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ ለነበሩ እንቅስቃሴዎች ወሳኝ ሚና ተጫውቷል። ይህ ታሪካዊ ዐሻራ ኢትዮጵያን የጥቁሮች ኩራት፣ ትግል እና ራስን የመቻል ምልክት እንድትሆን አስችሏታል።
የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲና
አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት ዋና መቀመጫ መሆኗ ኢትዮጵያ የአኅጉሪቷ የዲፕሎማሲ ማዕከል ሆና እንድትቀጥል አስችሏል።
እ.አ.አ በ1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት) ታሪካዊ ምሥረታ የተካሄደው በኢትዮጵያ ነው። ኢትዮጵያ ከድርጅቱ መሥራች ሀገራት መካከል አንዷ ናት። ይህም የአፍሪካ የጋራ የፖለቲካ ድምጽ እንድትሆን ምክንያት ሆኗል።
የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሴኤ) እና ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ተቋማት የሚገኙባት ኢትዮጵያ፤ በዲፕሎማሲው ምክክር እና ውሳኔ ሰጪነት ውስጥ ያላትን ማዕከላዊ ሚና የበለጠ የሚያጠናክር ነው።
የፓን አፍሪካኒዝም ድምጽ
ኢትዮጵያ በቅኝ አለመገዛቷ ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ሥር መስደድ ወሳኝ ነው። በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ለአፍሪካ አንድነት እና የጋራ ምላሽ አጥብቃ ስትሞግትም ቆይታለች። በአፍሪካ ኅብረት እና በተለያዩ መድረኮች ኢትዮጵያ የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካውያን መፈታት አለባቸው የሚለውን እሳቤ ለማስረጽ አበክራ እየሠራች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ተኮር መፍትሔዎች ከቃላት ባለፈ በአኅጉራዊ የትሥሥር አጀንዳዎች፣ ሰላም እና ደኅንነት ማዕቀፎች እንዲሁም የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ፈተናዎች እንዲፈቱ ድጋፏን በመስጠት ቁርጠኝነቷን አሳይታለች።
የአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነትንም በፍጥነት አጽድቃ ወደ ሥራ ማስገባቷ የዚሁ አንድ ማሳያ ነው።
ሰላም ማስከበር እና ቀጣናዊ መረጋጋት
ኢትዮጵያ በቀጣናዊ ሰላም እና መረጋጋት ስትራቴጂካዊ ሚና እየተወጣች ነው። በዚህም መሠረት ለተባበሩት መንግሥታት እና የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ከፍተኛ አስተዋጽዖ በማድረግ ከአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚውን ድርሻ ትይዛለች።
ሶማሊያ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳንን ጨምሮ ግጭት ባለባቸው የአፍሪካ ሀገራት ወታደሮቿን በመላክ ለሰላም እና ደኅንነት ያላትን ሚና በተግባር ገልጣ አሳይታለች።
የተባበሩት መንግሥታትም ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር እየተወጣች ላለው ሚና ምሥጋናውን ማቅረቡ ይታወቃል። ኢትዮጵያ በቀጣናው ሀገራት ያሉ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የተወጣችው የእርቅ እና የዲፕሎማሲ ሚናም ተጠቃሽ ነው።
የኢኮኖሚ እድገት እና ቀጣናዊ ትሥሥር
ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በአፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት መካከል በዋናነት ትጠቀሳለች።
በ2017 ዓ.ም ማብቂያ የተመረቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና በግንባታ ላይ የሚገኘው ኮይሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከግዙፍ መሠረተ ልማትነታቸው ባለፈ ቀጣናዊ ትሥሥር በማረጋገጥ ረገድ ወሳኝ ሚና አላቸው። ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የኢነርጂ የስኅበት ማዕከል እንድትሆን አድርጓታል።
ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት የምትሸጠው ኢነርጂ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትብብርን የሚያሳልጥ ነው።
የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መንገድን ጨምሮ የመንገድ መሠረተ ልማቶች እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢትዮጵያን የቀጣናዊ ትሥሥር ማዕከል እንድትሆን እያደረጓት ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት እየተከናወነ ያለው አረንጓዴ ዐሻራም፤ ኢትዮጵያን የአረንጓዴ ትብብር እና የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ተምሳሌት ማድረግ ችሏል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች ትገኛለች።
የባህል እና የሥልጣኔ አስተዋጽዖ
ኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክ፣ ቱባ ባህል እና ብዝኃነት መገለጫዋ ናቸው። የቋንቋ ብዝኃነት በአፍሪካ ውስጥ ገራገር የዲፕሎማሲ ኃይል (Soft Power) እንዲኖራት አስተዋጽዖ አድርጓል።
የኢትዮጵያ የሀገርነት ታሪክ እና የሥልጣኔ ትርክት አፍሪካ ያሏትን ጥልቅ የታሪክ ሥሮች ይበልጥ አጉልቶ የሚያሳይ ነው። የኢትዮጵያ ብዝኃ ማንነቶች፣ ሀገር በቀል ዕውቀቶች እና አስደማሚ የሥነ-ሕንጻ ሥራዎች በአፍሪካ ባህል እና ሥልጣኔ ውስጥ ያላቸው ሚና ትልቅ ነው።
ኢትዮጵያ አሁንም በአፍሪካ አንድነት እና መረጋጋት ውስጥ እንደ ቁልፍ ምሰሶ ትታያለች። በአኅጉሪቱ ውስጥ ያላት ድርሻ በታሪክ ሥር የሰደደ እና አሁን ባለው ዘመን በዲፕሎማሲ፣ በሰላም ግንባታ እና ልማት ሥራ በግልጽ ጎልቶ ይታያል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የፖለቲካ መዲና እንዲሁም የአይበገሬነት እና የነጻነት ምልክት ናት። አፍሪካ አንድነቷን ለማረጋገጥ፣ የተረጋጋ አኅጉር ለመፍጠር እና በራስ ዐቅም ነገሮችን የመከወን ጉዞ ትልም ውስጥ የኢትዮጵያ ድርሻ ቁልፍ ነው።
39ኛው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ “ዘላቂ የውኃ ኑረትና ንጽህና ሥርዓት፤ ለአጀንዳ 2063 ስኬት” በሚል መሪ ሐሳብ ዛሬና ነገ በኅብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ይካሄዳል።
ጉባዔው ኢትዮጵያ አኅጉራዊ የፖለቲካ እና ዲፕሎማሲያዊ መድረክ መሆኗን ዳግም የምታሳይበት ነው።