ሊቨርፑል፣ ባርሴሎና፣ ማንችስተር ሲቲ፣ ቼልሲ፣ ቶተንሃም ሆትስፐርስ እና ስፖርቲንግ ሊዝበን ጥሎ ማለፉን ተቀላቀሉ - ኢዜአ አማርኛ
ሊቨርፑል፣ ባርሴሎና፣ ማንችስተር ሲቲ፣ ቼልሲ፣ ቶተንሃም ሆትስፐርስ እና ስፖርቲንግ ሊዝበን ጥሎ ማለፉን ተቀላቀሉ
አዲስ አበባ፤ ጥር 21/2018 (ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የመጨረሻ ዙር መርሐ-ግብር ዛሬ ማምሻውን 18 ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሰዓት ተደርገዋል።
በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሊቨርፑል ካራባግን 6 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል።
አሌክሲስ ማካሊስተር ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር፤ ፍሎሪያን ዊትዝ፣ መሐመድ ሳላህ፣ ሁጎ ኢኪቲኬ እና ፌዴሪኮ ኪዬዛ ቀሪዎቹን ጎሎች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ወደ ጥሎ ማለፍ በቀጥታ የሚያልፉ ክለቦች የሚለዩባቸው ተጠባቂ ጨዋታዎች
ሊቨርፑል በ18 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ በቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፍ ገብቷል።
ቶተንሃም ሆትስፐርስ በራንዳል ኮሎ ሙዋኒ እና ዶምኒክ ሶላንኪ ግቦች ኢንትራክት ፍራንክፈርትን 2 ለ 0 አሸንፏል።
ስፐርስ በ17 ነጥብ አራተኛ ደረጃን በመያዝ ጥሎ ማለፉን ተቀላቅሏል።
በሌላ መርሐ-ግብር ባርሴሎና ኮፐንሃገንን 4 ለ 1 አሸንፏል። ቡድኑ በ16 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ 16 ውስጥ ገብቷል።
እንዲሁም ቼልሲ ናፖሊን 3 ለ 2 ከሜዳው ውጪ በማሸነፍ በተመሳሳይ 16 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ ስድስተኛ ደረጃን ይዞ ጥሎ ማለፍ መግባቱን አረጋግጧል።
የፖርቹጋሉ ስፖርቲንግ ሊዝበን አትሌቲኮ ማድሪድ 3 ለ 2 በማሸነፍ በ16 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ይዞ በማጠናቀቅ በቀጥታ ጥሎ ማለፍ መግባት ችሏል።
በተመሳሳይ ማንችስተር ሲቲ ጋላታሳራይን 2 ለ 0 በማሸነፍ በ16 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን በመያዝ 16 ውስጥ ገብቷል።
ቤኔፊካ በስታዲዮ ደ ሉዝ በተካሄደ ጨዋታ ሪያል ማድሪድን 4 ለ 2 አሸንፏል።
አንድሬስ ስጄልዴሩፕ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር አናቶሊ ቶርቢን በጨዋታ እና አንጄሊስ ፓቭሊዲስ በፍጹም ቅጣት ምት ቀሪዋን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ኪሊያን ምባፔ ሁለቱን ግቦች ለሪያል ማድሪድ ከመረብ ላይ አሳርፏል።
በጨዋታው ላይ ራውል አሴንሲዮ እና ሮድሪጎ ከሪያል ማድሪድ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብተዋል።
በጨዋታው ላይ የቤኔፊካው ግብ ጠባቂ አናቶሊ ቶርቢ በ98ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብ የቀየረበት ሁኔታ በተለየ አጋጣሚ የሚነሳ ነው።
ውጤቱን ተከትሎ የ15 ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ሪያል ማድሪድ በ15 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀ ሲሆን፤ ወደ ጥሎ ማለፍ ለመግባት የማጣሪያ ጨዋታ ያደርጋል።
ቤኔፊካ በዘጠኝ ነጥብ 24ኛ ደረጃን በመያዝ ለጥሎ ማለፍ ማጣሪያ አልፏል።
የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ፒኤስጂ ከኒውካስል ዩናይትድ አንድ አቻ ተለያይተዋል።
ቪቲንሃ ለፒኤስጂ፣ ጆሴፍ ዊሎክ ለኒውካስል ዩናይትድ ግቦቹን አስቆጥረዋል። የፒኤስጂው ኡስማን ደምበሌ ፍጹም ቅጣት ምት ስቷል።
ፒኤስጂ እና ኒውካስል ዩናይትድ በተመሳሳይ በ14 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው 11ኛ እና 12ኛ ደረጃን በመያዝ ለጥሎ ማለፍ ማጣሪያ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።
ኢንተር ሚላን፣ ጁቬንቱስ፣ አትሌቲኮ ማድሪድ፣ አትላንታ፣ ባየር ሊቨርኩሰን፣ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ፣ ሞናኮ፣ ጋላታሳራይ፣ ካራባግ፣ ኦሎምፒያኮስ እና ቦዶ ግሊምት ሌሎችም ለጥሎ ማለፍ ማጣሪያ ያለፉ ክለቦች ናቸው።
አርሰናል እና ባየር ሙኒክ አስቀድመው ጥሎ ማለፍ መግባታቸውን ያረጋገጡ ክለቦች ናቸው።
አርሰናል በመጨረሻ ጨዋታው ካይራት አልማቲን 3 ለ 2 አሸንፏል።
ቪክቶር ዮኮሬስ፣ ካይ ሃቨርትዝ እና ጋብርኤል ማርቲኔሊ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ሪካርዲኒዮ በጨዋታ እና ጆርጂኒዮ በፍጹም ቅጣት ምት ለካይራት ጎሎቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
አርሰናል በ24 ነጥብ አንደኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። በአዲሱ የውድድር ፎርማት ስምንት ተከታታይ ጨዋታዎችን ያሸነፈ የመጀመሪያው ክለብ ሆኗል።
የካዛኪስታኑ ካይራት አልማቲ በአንድ ነጥብ የመጨረሻውን 36ኛ ደረጃን ይዞ ከውድድሩ ተሰናብቷል።
ባየር ሙኒክ ፒኤስቪ አይንድሆቨንን በጀማል ሙሲያላ እና ሃሪ ኬን ግቦች 2 ለ 1 አሸንፏል።
ኢስማኤል ሳይባሪ ለፒኤስቪ ብቸኛውን ጎል አስቆጥሯል። ሳይባሪ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ የነበረ ተጫዋች ነው።
ባየር ሙኒክ በ21 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር በዘንድሮው ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል ፎርማትን በማስቀረት 36 ክለቦች በአራት ቋቶች (Pots) በመከፋፈል እንዲጫወቱ የሚያደርግ አዲስ አሰራር ከባለፈው የውድድር ዓመት አንስቶ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።
ከ36 ክለቦች መካከል በስምንት ጨዋታዎች የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ስምንት ቡድኖች በቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፉ ገብተዋል።
ቀሪዎቹ ስምንት ወደ ጥሎ ማለፉ የሚገቡ ቡድኖች በሁለት የማጣሪያ ዙሮች ተጫውተው ወደ 16ቱ ያልፋሉ።
በሻምፒዮንስ ሊጉ ከ9ኛ እስከ 24ኛ ደረጃ ይዘው የሚያጠናቅቁ ክለቦች በማጣሪያ ወደ ጥሎ ማለፍ ለመግባት ይጫወታሉ።
ከ25ኛ እስከ 36ኛ የሚያጠናቅቁ ቡድኖች ከውድድሩ ተሰናብተዋል። ናፖሊ፣ ማርሴይ፣ ኢንትራክት ፍራንክፈርት፣ አያክስ፣ ፓፎስ፣ ዩኒየን ሴይንት ጂልዋ፣ ኮፐንሃገን፣ አትሌቲኮ ቢልባኦ፣ ስላቪያ ፕራግ፣ ቪያሪያል፣ ፒኤስቪ አይንድሆቨን እና ካይራት አልማቲ ከውድድሩ የተሰናበቱ ክለቦች ናቸው።
ከጥሎ ማለፉ አንስቶ ያለው የውድድር ፎርማት ከዚህ ቀደም ከነበረው ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው።