ቀጥታ፡

በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ወደ ጥሎ ማለፍ በቀጥታ የሚያልፉ ክለቦች የሚለዩባቸው ተጠባቂ ጨዋታዎች

አዲስ አበባ፤ ጥር 20/2018 (ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ወደ ጥሎ ማለፍ በቀጥታ የሚያልፉ ክለቦች የሚለዩባቸው ተጠባቂ ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ።

 

‎የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የመጨረሻ ዙር መርሐ-ግብር ዛሬ ይካሄዳል። 

በዕለቱ 18 ጨዋታዎች በተመሳሳይ ምሽት አምስት ላይ ይደረጋሉ። 

በስታዲዮ ደ ሉዝ ቤኔፊካ ከሪያል ማድሪድ ይጫወታሉ። ቤኔፊካ በስድስት ነጥብ 29ኛ፣ 15 ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ሪያል ማድሪድ በ15 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። 

ሪያል ማድሪድ ማሸነፍ በቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፉ ያስገባዋል። አቻ ማውጣትም ሊያሳልፈው የሚችልበት እድል ሰፊ ነው። 

ሊቨርፑል ከካራባግ በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም ይጫወታል። 

ከሰባት ጨዋታዎች 15 ነጥብ ያገኘው ሊቨርፑል በ15 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል። ካራባግ በ10 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዟል። 

እንደ ሪያል ማድሪድ ሊቨርፑል ካሸነፈ በቀጥታ 16 ውስጥ ይገባል። አቻ ከወጣ በሂሳባዊ ስሌት የማለፍ እድል ይኖረዋል።

ኢንትራክት ፍራንክፈርት ከቶተንሃም ሆትስፐርስ ጋር ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በ14 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቶተንሃም ሆትስፐርስ ማሸነፍ ወደ ጥሎ ማለፍ ያስገባዋል። አቻ መውጣት የሌሎች ቡድኖችን ውጤት እንዲጠብቅ ያደርገዋል።

የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ፒኤስጂ ከኒውካስትል ዩናይትድ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

ፒኤስጂ እና ኒውካስትል ዩናይትድ በተመሳሳይ 13 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ስድስተኛ እና ሰባተኛ ደረጃን ይዘዋል።

የሁለቱም ቡድኖች ወደ ጥሎ ማለፉ የመቀላቀል ሂሳባዊ ስሌት ተመሳሳይ ነው። ያሸነፈ ቡድን 16 ውስጥ ይገባል።

ናፖሊ ከቼልሲ የሚያደርጉት ጨዋታም ትኩረት ስቧል። 

የጣልያኑ ክለብ ናፖሊ በስምንት ነጥብ 25ኛ ደረጃን ይዟል። ቼልሲ በ13 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ናፖሊ በቀጥታ የጥሎ ማለፍ የመግባት እድል የለውም። ማሸነፍ በሁለት የማጣሪያ ዙሮች ተጫውተው የሚያልፉ ክለቦችን እንዲቀላቀል ያደርገዋል።

ቼልሲ በሰፊ የግብ ልዩነት ማሸነፍ ማንንም ሳይጠብቅ ወደ ጥሎ ማለፍ እንዲገባ ያደርገዋል። 

ባርሴሎና፣ ስፖርቲንግ ሊዝበን፣ ማንችስተር ሲቲ፣ አትሌቲኮ ማድሪድ እና አትላንታ በተመሳሳይ 13 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ከ9ኛ እስከ 13ኛ ደረጃን ይዘዋል።

አምስቱ ክለቦች ወደ ጥሎ ማለፍ ለመግባት ከማሸነፍ ባለፈ በነጥብ የሚበልጧቸውን ክለቦች ውጤት ይጠብቃሉ።

14ኛ እና ከዛ በታች ያሉ ክለቦች በቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፍ የመግባት እድላቸው እጅጉን የጠበበ ነው።

አርሰናል እና ባየር ሙኒክ አስቀድመው ወደ ጥሎ ማለፉ መግባታቸውን ያረጋገጡ ክለቦች ናቸው። 

አርሰናል ከካይራት አልማቲ እና ባየር ሙኒክ ከፒኤስቪ አይንድሆቨን ጋር ማምሻውን ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በዘንድሮው ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል ፎርማትን በማስቀረት 36 ክለቦች በአራት ቋቶች (Pots) በመከፋፈል እንዲጫወቱ የሚያደርግ አዲስ አሰራር ከባለፈው የውድድር ዓመት አንስቶ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል። 

ከ36 ክለቦች መካከል በስምንት ጨዋታዎች የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ስምንት ቡድኖች በቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፉ ይገባሉ።

ቀሪዎቹ ስምንት ወደ ጥሎ ማለፉ የሚገቡ ቡድኖች በሁለት የማጣሪያ ዙሮች ተጫውተው ወደ 16ቱ ያልፋሉ።

በሻምፒዮንስ ሊጉ ከ9ኛ እስከ 24ኛ ደረጃ ይዘው የሚያጠናቅቁ ክለቦች በማጣሪያ ወደ ጥሎ ማለፍ ለመግባት ይጫወታሉ።

ከ25ኛ እስከ 36ኛ የሚያጠናቅቁ ቡድኖች ከውድድሩ ይሰናበታሉ። ኢንትራክት ፍራንክፈርት፣ ስላቪያ ፕራግ፣ ቪያሪያል እና ካይራት አልማቲ ከውድድሩ የተሰናበቱ ክለቦች ናቸው። 

ከጥሎ ማለፉ አንስቶ ያለው የውድድር ፎርማት ከዚህ ቀደም ከነበረው ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም