ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሀገራዊ አቅም ማሳያና የብሔራዊ ኩራት መገለጫ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 16/2018 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሀገራዊ አቅም ማሳያና የብሔራዊ ኩራት መገለጫ መሆኑን የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል አከባበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ከፍተኛ እንግዶች በተገኙበት በድምቀት እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የምስረታ በዓሉን አስመልክቶም "ጥቁር አንበሳ" የተሰኘው አስደማሚ የአየር ላይ ትርዒት በመከናወን ላይ ነው።

የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ መርሃ ግብሩ የ90 ዓመት ክብረ በዓል ብቻ ሳይሆን፣ የዘጠኝ አስርት ዓመታት የጠንካራ ብሔራዊ አገልግሎትና ያልተቋረጠ የልህቀት ማሳያ ነው፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ላለፉት 90 ዓመታት የኢትዮጵያ የሉዓላዊነት ጽኑ ምሽግ ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ የአየር ኃይል መስራች መሆኗን፣ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎችን መደገፏንና የብሔራዊ ጥቅሟን የሚገዳደሩ ኃይሎችን አቅም ያከሸፈች መሆኗን ተናግረዋል፡፡

ይህ የ90ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልና የጥቁር አንበሳ የአየር ትርኢት የኢትዮጵያን የኩራት መገለጫነትና የበረራ ልህቀት በተግባር የሚያረጋግጥ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በአከባበሩ ላይ የአፍሪካና የሌሎች ሀገራት አየር ኃይል አዛዦች በመገኘታቸው ኩራት እንደሚሰማቸው የገለጹት ሌተናል ጀነራል ይልማ ለዚህ ስኬት ድጋፍ ላደረጉ አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡


 

የአየር ትርኢቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ገጽታ የሚገነባ መሆኑን ጠቅሰው፤ ካዴቶች ለህልማቸው እንዲተጉ፣ ዜጎችም በሀገራቸው የቴክኖሎጂ መጻኢ ዕድል እንዲተማመኑ የሚያደርግ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሀገራዊ አቅም ማሳያ፣ የብሔራዊ ኩራትና ዓለም አቀፋዊ ተፈላጊነትን ለማሳደግ ስትራቴጂካዊ መሣሪያ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

"ባለፈው እንኮራለን፤ በአሁኑ እንመራለን፤ የቀጣዩን እንቀርፃለን" ያሉት ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ፤ መርሃ ግብሩ የኢንዱስትሪ ሽግግርና የጋራ ትብብር ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በዓሉ የመሰረተ ልማት ግንባታ ስኬትን እንዲሁም የአራተኛውና አምስተኛው ትውልድ የአየር ኃይል አቅም መገለጫ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአየር ኃይል አባላት እንቅልፍ አልባ ሌሊቶችን በማሳለፍ የኢትዮጵያን አቅም በተግባር ስላሳዩ የላቀ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

የዓለም አቀፍ አጋሮች በዚህ መርሃ ግብር መሳተፋቸው ግንኙነታችንን በማጠናከር የጋራ ትብብራችንን ለማሳደግና አስተማማኝ የአየር ኃይል አቅም ለመገንባት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም