ሀገራዊ ምክክሩ ለደረሰበት ወሳኝ ምዕራፍ ስኬታማነት የሁሉም ዜጋ የነቃ ተሳትፎ የበለጠ መጠናከር አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ ለደረሰበት ወሳኝ ምዕራፍ ስኬታማነት የሁሉም ዜጋ የነቃ ተሳትፎ የበለጠ መጠናከር አለበት
አዲስ አበባ፤ ጥር 15/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ለደረሰበት ወሳኝ ምዕራፍ ስኬታማነት የሁሉም ዜጋ የነቃ ተሳትፎ የበለጠ መጠናከር እንዳለበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ የምክክር መድረክ ማካሄዱ ይታወቃል።
ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት ሀገራዊ ምክክሩ ታሪካዊ ዕድል ነው
በቀጣይም ትግራይ ክልል ቀሪ አጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታን በማከናወን ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለማካሄድ የዝግጅት ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ፣ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መሐመድ አብዶ እንዳሉት ምክክር ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር እጅግ አስፈላጊ አጀንዳ ነው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር በወሳኝ የምክክር ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በአጀንዳ ማሰባሰብ፣ በተሳታፊ ልየታና ግብዓት ማሰባሰብ ላይ ኮሚሽኑ ዋናውን ሀገራዊ ምክክር ለማካሄድ የሚበረታታ አስቻይ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክርም ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር አሰባሳቢ ትርክት ለመገንባት ምቹ መደላድል የሚፈጥር ወርቃማ ዕድል መሆኑን ነው ጨምረው ያብራሩት።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በመጨረሻው ምዕራፍ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ላስቀመጠው ወሳኝ ግብ ስኬታማነት የሁሉም ዜጋ ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አስገንዘብዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ለሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ስኬታማነት የሚጠበቅባቸውን ገንቢ ኃላፊነት እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
ሌላኛዋ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሙስሊማ ረሽድ በበኩላቸው፤ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መፍትሔ ለማበጀት ለምክክር መድረክ ቅድሚያ መስጠት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክርም በሃሳብ የበላይነት የተመሰረተ የፖለቲካ ባህል በመገንባት ዘላቂ ሀገራዊ መግባባትን በመፍጠር አንድነትን ለማጽናት ሁነኛ አማራጭ መሆኑን ገልጸዋል።
የምክክር ኮሚሽኑ ቀሪ የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ እንዲሁም ዋናውን ሀገራዊ ጉባኤ ለማካሄድ አስፈላጊ የአጀንዳ ልየታና ግብዓት የማሰባሰብ ዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም እንደምክር ቤት አባል ኮሚሽኑ ዓላማውን ለማሳካት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።