ቀጥታ፡

ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት ሀገራዊ ምክክሩ ታሪካዊ ዕድል ነው

ገንዳውኃ፤ ጥር 15/2018 (ኢዜአ)፡- ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ለሁላችንም የምትመች ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት ሀገራዊ ምክክሩ ታሪካዊ ዕድል ነው ሲሉ የሲቪክ ማኅበራት የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።


 

የገንዳውኃ ከተማ የሴቶች ልማት ማኅበር ሰብሳቢ ብዙዬ የሱፍ እንዳሉት፤ ቀደም ሲል እንደ ሀገር ችግሮችን ለመፍታት የሄድንባቸው መንገዶች ጉዳት አስከትለዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ ለደረሰበት ወሳኝ ምዕራፍ ስኬታማነት የሁሉም ዜጋ የነቃ ተሳትፎ የበለጠ መጠናከር አለበት

በመመካከር ችግሮችን ከመፍታት የተሻለ አዋጭ መፍትሔ አለመኖሩን ተገንዝበን፤ ይህን ታሪካዊ ዕድል በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።

የምክክር ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ የሁሉም ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሴቶች በንቃት እንዲሳተፉ እየሠራን ነው ብለዋል።


 

የምክክር ሂደቱ ግልጽ፣ አሳታፊና አካታች መሆኑን የገለጹት ደግሞ የገንዳውኃ ከተማ የአካል ጉዳተኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት መምህር ጌታ ታደሠ ናቸው።

የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ የሌለበት የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውጤታማ እንደማይሆን በመገንዘብ የምክክር ኮሚሽን ለሰጠው ትኩረት አመሥግነዋል።

በኢትዮጵያ የቆዩ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ምክክሩ ይዞት የመጣውን መልካም ዕድል ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉም ኃላፊዎቹ ኢዜአ ተናግረዋል።

በምክክር ሂደቱ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ለሀገር ሰላምና ዕድገት ግንባታ የድርሻችን እንወጣለን ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም