የገጠር መንገድ ግንባታው የአርሶአደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የበለጠ የሚያረጋግጥ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የገጠር መንገድ ግንባታው የአርሶአደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የበለጠ የሚያረጋግጥ ነው
ሐረር ፤ ጥር 14 /2018(ኢዜአ)፦በሐረሪ ክልል እየተከናወነ ያለው የገጠር መንገድ ግንባታ የአርሶአደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የበለጠ ለማረጋገጥ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ዑመር ገለጹ።
በሐረሪ ክልል ገጠሩን ከከተማ የሚያስተሳስር የ150 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታና ጥገና እየተከናወነ ይገኛል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር ለኢዜአ እንዳሉት፣ የገጠር መንገድ ግንባታው፣አርሶአደሩ ምርቱን በቀላሉ ወደ ገበያ እንዲያቀርብ ያግዛል።
የአርሶአደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የበለጠ ለማረጋገጥ የጎላ ሚና እንደሚኖረውም አንስተዋል።
በክልሉ የኢንቨስትመንት ፍቃድ የወሰዱ አልሚዎች የስራ እንቅስቃሴን በጥብቅ ዲሲፕሊን መምራት ይገባል
በከተማዋ እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት ከገጠሩ ጋር በማስተሳሰር ሞዴል የገጠር መንደሮችን ለመገንባት እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደሚያግዝም ነው ያነሱት።
የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ ፈቲህ ተውፊቅ በበኩላቸው፣ በተያዘው በጀት ዓመት በክልሉ ገጠርን ከከተማ የሚያስተሳስሩና የህብረተሰቡን ኑሮ የሚያሻሽሉ የመንገድ መሰረተ ልማቶች እየተከናወኑ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የአዳዲስ የገጠር መንገዶች ግንባታን ጨምሮ ነባሮቹን የማሻሻልና ሥራ በተያዘለት የጊዜ ገደብ በጥራት እንዲጠናቀቅም ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ የመንገዱ ግንባታ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚሰጣቸው ገልጸው፤ ለግንባታው አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የድሬ ጠያራ ወረዳ ሲጊቻ ቀበሌ ነዋሪ ሐሰን ዩስፌ፤ ምርታቸውን ከተማ ይዘው በመሄድ እንዲገበያዩና የተሻለ ጥቅም እንዲያገኙ የመንገዱ ግንባታ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ፉአድ ሙሳ በበኩላቸው፤ቀደም ሲል የነበረው መንገድ ጠባብና ለተሽከርካሪ ምልልስ አስቸጋሪ እንደነበር አስታውሰው፤ አዲስ እየተገነባ ያለው መንገድ ይህን ችግር በማቃለል የተሽከርካሪ ፍሰቱን ያሳልጣል ብለዋል።