በክልሉ የኢንቨስትመንት ፍቃድ የወሰዱ አልሚዎች የስራ እንቅስቃሴን በጥብቅ ዲሲፕሊን መምራት ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የኢንቨስትመንት ፍቃድ የወሰዱ አልሚዎች የስራ እንቅስቃሴን በጥብቅ ዲሲፕሊን መምራት ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ
አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2018(ኢዜአ)፦ በክልሉ የኢንቨስትመንት ፍቃድ የወሰዱ አልሚዎች የስራ እንቅስቃሴን በጥብቅ ዲሲፕሊን መምራት እንደሚገባ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ አስገነዘቡ።
የክልሉ ኢንቨስትመንት ቦርድ የኢንቨስትመንት ማዕድንና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ገምግሟል።
በቀረበው ሪፖርትም በክልሉ በኢንቨስትመንት ፍቃድ መሬት ወስደው ወደ ስራ ባልገቡ አልሚዎች ላይ ከማስጠንቀቂያ ጀምሮ እስከ ኢንቨስትመንት ፍቃድ ስረዛ ርምጃ መወሰዱ ተመላክቷል።
በመድረኩ አቶ ኦርዲን በድሪ እንዳሉት፤ ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር የክልሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንዲጎለብት መስራት ያስፈልጋል።
የኢንቨስትመንት ፍቃድ የወሰዱ አልሚዎች የስራ እንቅስቃሴን ልዩ ትኩረት በመስጠት በጥብቅ ዲሲፕሊን መምራት ይገባል ሲሉም ነው ያስገነዘቡት።
በክልሉ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለተሰማሩ አልሚዎች ድጋፍ ለማድረግ የክልሉ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው፤ ለአልሚዎች ስራ መቀላጠፍ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለይቶ ለመፍታት እንደሚሰራም ገልጸዋል።
ለኢንቨስትመንት መሬት ወስደው ወደ ስራ ባልገቡ አልሚዎች ላይ ክትትል በማድረግ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድም አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በተለይም በራሳቸው ይዞታ ላይ ለሚያለሙ ባለሃብቶች ቅድሚያ በመስጠት የመደገፍ ስራ እንደሚሰራ ማመልከታቸውን የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ለኢዜአ በላከው መረጃ አስታውቋል።
በተለይም በሆቴል፣ በማኑፋክቸሪንግና በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም ነው የገለጹት።
በክልሉ የተጀመረውን የኢንቨስትመንት ክትትል እና ቁጥጥር ስራ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።