በምዕራብ ወለጋ ዞን በ 487 ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ወለጋ ዞን በ 487 ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እየተከናወነ ነው
ጊምቢ፤ ጥር 14 /2018(ኢዜአ)፦ በምዕራብ ወለጋ ዞን በ487 ተፋሰሶች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
በምዕራብ ወለጋ ዞን ግብርና በጽህፈት ቤት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ፍቅሩ ብርሃኑ እንዳሉት፣ በዞኑ በ487 ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡
ባለፉት አመታት በዞኑ በተከናወኑ የተለያዩ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች በመጡ ተጨባጭ ለውጦች አርሶ አደሩን ተጠቃሚ በማድረጋቸው ለዘንድሮ ተፋሰስ ልማት ስራዎች በነቂስ ወጥተው እየተሳተፉ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡
በዞኑ ከ273 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሚሸፍን የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ መካሄድ ጀምሯል
በተለይም እየተከናወኑ ባሉ የተፋሰስ ልማት ስራዎች የእርከን ስራና ቀደም ብለው የለሙ ተፋሰሶች ከእንስሳትና ከሰው ንክኪ ነጻ እንዲሆኑ ጥበቃ ይደረግለታል ብለዋል።
በዞኑ በላሎሳቢ፣ በመነስቡ፣ በጊምቢና ሆማ ወረዳዎች በእስካሁኑ እንቅስቃሴ በእርከን ስራ የተሻለ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት በተፋሰስ ልማት መርሃ ግብር በተከናወኑት ስራዎች የተራቆቱ አካባቢዎች ወደ ልምላሜ መመለሳቸውን እና በዘንድሮው የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ምክንያት እንደሆናቸው የሚናገሩት ደግሞ አርሶ አደር አምቢሳ ጉዲና ናቸው፡፡
ልማቱ ቀደም ሲል በአፈር መሸርሸር ምክንያት ምርታማነት ቀንሶ የነበረው የእርሻ መሬታቸው አሁን ላይ ማገገሙን ጠቅሰዋል።
አርሶ አደር ከኔሳ አሙማ በበኩላቸው፤ ባለፉት አመታት በተከናወኑት የእርከንና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች በአካባቢያቸው ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም በዘንድሮ የበጋ ወራት የእርከን ልማት ስራዎች ላይ ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡