ቀጥታ፡

በዞኑ ከ273 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሚሸፍን የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ መካሄድ ጀምሯል

አምቦ፤ ጥር 6/2018(ኢዜአ)፦ በምዕራብ ሸዋ ዞን ከ273 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሚሸፍን የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ መካሄድ መጀመሩን የዞኑ አስተዳደር ገለጸ።

በዞን ደረጃ የሚካሄደው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በአምቦ ወረዳ  ኢላሙ ጎሮምቲ ቀበሌ በይፋ ተጀምሯል።

የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ የልማትና የዕድገት ግቦችን ለማሳካት እያገዘ ነው

የምዕራብ ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳደሪ አቶ አበበ ጨመዳ  በወቅቱ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ባለፉት አመታት በተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የአፈር ለምነት እንዲመለስ አድርጓል።


 

በዚህ የበጋ ወራትም ተግባሩን በማስቀጠል ለሁለት ወራት የሚቆይ የተቀናጀ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ዘመቻ የተለያዩ  የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ  ከ273 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ  እንደሚከናወን  ተናግረዋል፡፡ 

በዘመቻ መልክ በሚካሄደው በዚህ ስራ ከ600 ሺህ በላይ የዞኑ ነዋሪዎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አስረድተዋል።


 

የምዕራብ ሸዋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አብዲሳ ሀይሉ በበኩላቸው፤ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ስራውን ውጤታማ ለማድረግ በየደረጃው ላሉ የግብርና ባለሙያዎች፣ ለአርሶ አደሮች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡


 

የአምቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሰረት ጉዲሳ እንዳሉት፤ ባለፉት ጊዜያት በወረዳው በተከናወኑት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች ከልማት ወጪ የነበሩ አካባቢዎች  ዳግም ወደ ልማት ገብተዋል።


 

ህብረተሰቡም ጥቅሙን በመረዳቱ  በተፋሰስ ልማቱ  በነቂስ  ወጥቶ እየተሳተፈ መሆኑን ጠቅሰው በወረዳው ከ2 ሺህ 700  ኪሎ ሜትር መሬት  በላይ  የእርከን፣ የስነ-ህይወታዊና የስነ-አካላዊ ስራዎች ይከናወናል ብለዋል።

የአምቦ ወረዳ ኢላሙ ጎሮምቲ ቀበሌ አርሶ አደሮች የተፋሰስ ልማት ስራው ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት  የእርሻ ማሳቸው ለም አፈር በጎርፍ በመጠረጉ ምርታማነታቸው መቀነሱን ጠቁመዋል።


 

ችግሩን ለማቅረፍም በየአመቱ በሚከናወነው የተቀናጀ  የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ  መሳተፋቸውን አስረድተዋል። 

በተፋሰስ ልማቱ ባለፉት ዓመታት የተሰሩ አፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የአፈር መሸርሸርን አስቀርቷል ብለዋል።ይህም  የሰብል ምርታቸው  እንዲጨምር ማድረጉን  ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም