በተጠባቂው የደርቢ ጨዋታ ማንችስተር ዩናይትድ ማንችስተር ሲቲን አሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
በተጠባቂው የደርቢ ጨዋታ ማንችስተር ዩናይትድ ማንችስተር ሲቲን አሸነፈ
አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ተጠባቂ መርሐ-ግብር ማንችስተር ዩናይትድ ማንችስተር ሲቲን 2 ለ 0 አሸንፏል።
በኦልድትራፎርድ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ብራያን ምቡዌሞ በ65ኛውና ፓትሪክ ዶርጉ በ76ኛው ደቂቃ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ምቡዌሞ በዩናይትድ ማልያ ሰባተኛ የሊግ ጎሉን ከመረብ ላይ አሳርፏል።
በጨዋታው ላይ ማንችስተር ዩናይትድ ብልጫ ወስዶ የተጫወተ ሲሆን፤ ተጨማሪ ግቦችን የማስቆጠር እድሎችን ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
የዓለም አይኖች ያረፉበት ተጠባቂው የማንችስተር ደርቢ
ማንችስተር ሲቲ ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴ አድርጓል። ይህን ተከትሎም 198ኛው የማንችስተር ደርቢ በማንችስተር ዩናይትድ አሸናፊነት ተጠናቅቋል።
በሊጉ 10ኛ ድሉን ያስመዘገበው ዩናይትድ በ35 ነጥብ ደረጃውን ከሰባተኛ ወደ አራተኛ ከፍ አድርጓል።
በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ አምስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ማንችስተር ሲቲ በ43 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
ከሊጉ መሪ አርሰናል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት የማጥበብ እድል አምክኗል። ቡድኑ ባለፉት አራት ጨዋታዎች አላሻነፈም።
የሊጉ መሪ አርሰናል ዛሬ ማምሻውን ኖቲንግሃም ፎረስት ካሸነፈ ከሲቲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ዘጠኝ ከፍ ያደርጋል።