የአውሮፓ ሕብረት እና አባል አገሮቹ የኢትዮጵያ አስተማማኝ አጋሮች ናቸው - ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የአውሮፓ ሕብረት እና አባል አገሮቹ የኢትዮጵያ አስተማማኝ አጋሮች ናቸው - ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2018(ኢዜአ)፦የአውሮፓ ሕብረትና አባል አገሮቹ የኢትዮጵያ አስተማማኝ አጋሮች መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ገለጹ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአውሮፓ የውጭ ጉዳይ አገልግሎት የፖለቲካ ጉዳዮች ምክትል ዋና ፀሐፊ ኡሎፍ ስኩጊን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብራቸውን ለማጠናከር የጋራ ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ
በውይይታቸውም የአውሮፓ ሕብረትና አባል አገሮቹ የኢትዮጵያ አስተማማኝ አጋሮች መሆናቸውን የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ግንኙነቱ በጋራ ዕሴቶች እና ተስፋዎች ላይ የተመሰረተ ወሳኝ አጋርነት መሆኑንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ ውህደት የምታደርገውን ጥረት ያነሱት ሚኒስትሩ እንቅስቃሴው ከአውሮፓ ህብረት ግሎባል ጌትዌይ ኢኒሼቲቭ(Global Gateway initiative) ጋር የሚጣጣም መሆኑን ገልጸው በቀጣናው ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ውህደትን ለማሳደግ ያላትን ቁርጠኝነትም ተናግረዋል።
እየተከናወነ ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በፈጠረው ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድል የአውሮፓ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የበለጠ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ኡሎፍ ስኩጊን በበኩላቸው ህብረቱ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የሚያደርገውን ድጋፍና ስትራቴጂያዊ አጋርነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ የኮፕ 32 አስተናጋጅ ሆና በመመረጧ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን የኢትዮጵያን የልማት ውጥኖች ከግብ ለማድረስ ህብረቱ አስፈላጊውን ትብብር ያደርጋል ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ እደሚያመለክተው በውይይታቸው ሁለቱም ወገኖች በጋራ ጥቅም ላይ በሚያተኩሩ ጉዳዮች አብረው ለመስራት ተስማምተዋል።