ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብራቸውን ለማጠናከር የጋራ ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብራቸውን ለማጠናከር የጋራ ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት የንግድ፣ ኢንቨስትመንትና የኢኮኖሚ ትብብራቸውን ለማጎልበት እንደሚሰሩ አስታወቁ።
የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት ኢንቨስትመንት ፎረም ዛሬ በፈረንሳይ ፓሪስ መካሄድ ጀምሯል።
በመክፈቻው ስነ ስርዓት ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)፣ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ፣ የአውሮፓ ኮሚሽን የአፍሪካ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ጌዛ ስትራመር፣ የፈረንሳይ የወጪ ንግድ እና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር መልዕክተኛ ኒኮላስ ፎርሲየር፣ የሜዴፍ ኢንተርናሽናል ምክትል ፕሬዝዳንት ፋብሪስ ላሳች፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ባለሀብቶች እና የንግድ መሪዎች ተገኝተዋል።
ፎረሙ በኢትዮጵያ እና አውሮፓ ህብረት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትብብር ማጠናከርና አዳዲስ የኢንቨስትመንት እድሎችን መጠቀም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ በፎረሙ ላይ የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም በዝርዝር አስረድተዋል።
ሪፎርሙ የግል ኢንቨስመንት መሳብ እና ኢትዮጵያ ከዓለም ኢኮኖሚ ጋር ያላትን ትስስር የበለጠ ማጠናከርን ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
በፎረሙ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉ ባለስልጣናት የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት የኢኮኖሚ ትብብር እያደገ መምጣቱን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል እያከናወነቻቸው ያሉ ስራዎችንም አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ምቹነትን ለማሻሻልና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብን አላማ በማድረግ እያደረገቻቸው ያሉ የመንግስት እና የግሉ ዘርፍ ምክክሮች መልካም የሚባሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በኢንቨስትመንት ፎረሙ ላይ ኢትዮጵያ በግብርና ንግድ፣ የታዳሽ ኃይል፣ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና መሰረተ ልማትን ጨምሮ ቁልፍ የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት እድሎች ቀርበዋል።
በፎረሙ የአውሮፓ ህብረት የ"ግሎባል ጌትዌይ ፓርትነርሺፕ" ማዕቀፍ ያለው ጠቀሜታም ተነስቷል።
"ግሎባል ጌትዌይ ፓርትነርሺፕ" በአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን የሚመራ የአውሮፓ ህብረት ዓለም አቀፍ ኢኒሼቲቭ ሲሆን ህብረቱ ከተለያዩ ሀገራት በዲጂታላይዜሽን፣ በታዳሽ ኃይል፣ በስርዓተ ምግብ፣ በጤና፣ በዘላቂ ግብርና፣ ሰላምና ደህንነትን ጨምሮ በቁልፍ ዘርፎች ያለውን ትብብርና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ነው።
ማዕቀፉ የሁለቱ ወገኖች ትብብር ለማጠናከርና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽንና ዘላቂ እድገት የሚውል የአውሮፓን ኢንቨስትመንት ለማሰባሰብ እንደሚያግዝ ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት ኢንቨስትመንት ፎረም በኢትዮጵያ ተቋማትና በአውሮፓ ኩባንያዎች መካከል በኢኖቬሽን፣ በእሴት መጨመርና የጋራ ብልጽግናን መደገፍ ላይ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር የሚያስችል ስትራቴጂካዊ ማዕቀፍ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።
ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት የንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ለማጎልበት ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ እንደሆነም ገልጿል።